በቦረና የማኅበረሰቡን ሕይወት እንዲቀይሩ የተገነቡት 18 ሰው ሠራሽ ሐይቆች።

11

ብዙዎች ቦረናን በአዕምሯችን ስናስብ የሚመጣው ከአርብቶ አደርነት ሕይወት ባሻገር ድርቅ ሊኾን ይችላል።

ምክንያቱም በተደጋጋሚ በድርቅ በሚጠቃው የምሥራቅ አፍሪካ ከፊል በርሃማ ቀጣና አካል ስለኾነ ነው።

ቦረና አልፎ አልፎ በድርቅ ከመጠቃቱ ውጭ ለም አፈር እና በቂ ውኃ የሚያገኝ አርብቶ አደር ብሎም ውብ ባሕል ያለው የኦሮሞ ገዳ መሠረት አካባቢ ነው። አካባቢው ወርቅን ጨምሮ ሳፋየር ኤሜራልድ እና መሰል ውድ ማዕድናትም ባለቤት ነው።

በአዲሱ የኦሮሚያ አደረጃጀት በደቡብ ኦሮሚያ ዞን ይገኛል። መንግሥት በሰጠው ትኩረትም በዞኑ 23 ሰው ሠራሽ ሐይቆች የተገነቡ ሲኾን በቦረና ብቻ 18 ሐይቆች ተገንብተዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ታዲያ የማኅበረሰቡን ሕይወት፣ የሀገርን ገጽታ ቀያሪ ፕሮጀክቶች ናቸው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች “ፊና” ተብለው የተሰየሙ ሲኾን ትርጓሜውም በረከት እንደማለት ነው።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል አሚኮ ስለተገኘበት አንዱ ፕሮጀክት ብቻ እንንገራችሁ። በጉመሌ ወረዳ የሚገኘው ሰው ሠራሽ ሐይቅ አንዱ ሲኾን ሐይቁ 22 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የመያዝ አቅም ያለው እና በግማሽ ቢሊዮን ብር በጀት የተጠናቀቀ ፕሮጀክት መኾኑን የጉመሌ ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ ካራ ዳዲ (ዶ.ር) ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ለእንስሳት መጠጥ፣ ለመስኖ፣ ለባሕላዊ መኖ ጥበቃ እና ለዓሣ ርባታ የሚያገለግል ሲኾን ድርቅ ቢከሰት እንኳ ውኃ ይዞ ለሁለት ዓመት የመቆየት አቅም አለው። በሐይቁ 3ሺህ 400 በላይ አርሶ አደሮችንም ተጠቃሚ ያደርጋል።

ከዚህ በፊት እንስሳትን ውኃ ለማጠጣት የ3 ሰዓት ጉዞ ይፈልግ የነበረው እንግልት ተቀርፏል።

የአካባቢው አርብቶ አደሮች ከ3 ዓመት በፊት ተከስቶ በነበረው ድርቅ ያለቁ ከብቶቻቸውን እያስታወሱ ቢተክዙም ዛሬ ግን ፍፁም እንዳይደገም ያደረገ ፕሮጀክት በራቸው ላይ በመገንባቱ መደሰታቸውን አጫውተውናል።

ዛሬ እንደ “ፊና “ዓይነት ፕሮጀክቶች በመላው ኢትዮጵያ እንዲገነቡላት ሀገር ትሻለች። ፕሮጀክቶቹ የአርብቶ አደሩን እና የአርሶ አደሩን ሕይወት ቀይረው ኢትዮጵያን ሥልጡን ዜጎቿ የሚኮሩባት ሀገር ያደርጓታል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#አዲስ_አበባ #ኅዳር_09_2019_ዓ_ም

✍️:- በአንዱዓለም መናን (ከቦረና ያቤሎ)

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous article‎116 ዘመናዊ ካሜራዎች የተገጠሙለት የባሕር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲዬም እውነታዎች!