‎🏟️ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከስፖርት መድረክነት ባሻገር ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ

5

ባሕር ዳር በየጊዜው የሚመጥናትን ከፍታ ዕውን ለማድረግ ከምታከናውናቸው በርካታ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መካከል አንዱ የኾነው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ዛሬ ከሀገር አቀፍ ጨዋታዎች ባለፈ የአህጉር አቀፍ ውድድሮች የስበት ማዕከል ኾኗል።
‎
‎የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሴኔጋል አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ ወደ ውድድር የተመለሰው ስታዲየሙ ሞዛምቢክን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ እንግዶችን ማስተናገዱ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ የሀገሪቱን መልኮች ለመግለጥ እና ከተማዋን የሰላም፣ የዕድገት እና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ጉልህ ሚና አለው።
‎
‎እንደ ኳታር እና ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ ያሉ ሀገራት የዓለም ዋንጫን እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ሲያስተናግዱ ኢንቨስትመንታቸውን በዘላቂ መሠረተ ልማት፣ በዘመናዊ ትራንስፖርት፣ በሆቴሎች እና በስታዲየሞች ላይ በማድረግ ከተሞቻቸውን ቀጣይነት ያለው የቱሪዝም መዳረሻ አድርገዋል።
‎
‎የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም መገንባትም ከሀገር ውስጥ ባሻገር ዓለም አቀፍ እንግዶች ለመቀበል የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች እንዲከናወኑ ጉልበት ይኾናል፤ እየኾነም ነው።
‎
‎ከተማዋ አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ስታስተናግድ ዓለም አቀፍ ትኩረትን በመሳብ የኢትዮጵያን ሰላም፣ እንግዳ ተቀባይነት እና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች ለውጭ ቱሪስቶች እና ባለሀብቶች በማሳየት ረገድ እንደ ወርቃማ መስኮት ያገለግላል።
‎
‎ትላልቅ ስፖርታዊ ዝግጅቶች መደረጋቸው የከተማዋን መሠረተ ልማቶች ማለትም ሆቴሎች፣ መንገዶች፣ መገናኛዎች እና የስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲሻሻሉ እና የዓለም አቀፍ ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ከፍተኛ ግፊት ይፈጥራሉ።
‎
‎የኢኮኖሚ እና የልማት እንቅስቃሴው ከከተማዋ ገጽታ ግንባታ ባሻገር በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች እና ነዋሪዎች ከዓለም አቀፍ እንግዶች ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር የባህል ልውውጥን የሚያጎለብት እና የከተማዋን ማኅበራዊ ንቃተ-ህሊና ከፍ የሚያደርግ ነው።
‎
‎በአጠቃላይ እንደነዚህ አይነት ጨዋታዎች የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በዓለም መድረክ ላይ በድምቀት ከፍ አድርጎ ለማስቀጠል ያስችላል።
‎
‎✍️ በስማቸው አጥናፍ
‎
‎#AMECO #AFCON #sports #Bahir_Dar #Ethiopia

Previous articleየአየር ንብረት ፋይናንስ ለታዳጊ ሀገራት ቅድሚያ ፍላጎቶች ምላሽ በሚሰጥ መልኩ እንዲቀርብ ጥሪ ቀረበ።
Next articleባሕር ዳር ከተማን ያደመቀው ድጋፍ!