
ኢትዮጵያ የነገ መሠረቷን ዛሬ ላይ በፅናት እየገነባች ነው።
የዓባይን ወንዝ ለልማት ባዋለችበት ጉባ ላይ ከተበሰሩት የ30 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የኾነው የኒውክሌር ቴክኖሎጂ የሀገሪቱን ዘላቂና አስተማማኝ ኢነርጂ መጻኢ ዕጣ ፈንታ በውል የሚወስን ታሪካዊ ምዕራፍ ኾኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ቀድማ መጀመር የነበረባት፣ ነገር ግን ዘግይቶም ቢኾን በዚህ ትውልድ ዕውን መኾን የጀመረውን የኑክሌር ቴክኖሎጂ እንደ ማዕከላዊ የብሔራዊ ልማት ምሰሶ አስቀምጠውታል።
ዋናው ግቡም የኀይል ደኅንነትን ማጠናከር፣ የኢንዱስትሪ ዕድገትን ማፋጠን፣ የዲጂታል መሠረተ ልማትን መደገፍ እና እምቅ አቅምን ወደ ተጨባጭ ልማት መቀየር ነው።
ኒውክሌር እንደ ውኃ፣ ሶላር እና ንፋስ ካሉ ወቅታዊ የአየር ንብረት መዋዠቅ ተጽዕኖ ከሚደርስባቸው ተለዋዋጭ የኀይል ምንጮች በተለየ መልኩ ቋሚ፣ የተረጋጋ እና ከፍተኛ ኀይል የማመንጨት አቅም አለው። ይህም ለኢንዱስትሪዎች ዕድገት እና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር አጋዥነቱ ከፍ ያለ ይኾናል።
የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ፋይዳ በኀይል ማመንጨት ብቻ ሳይወሰን በጤና፣ በግብርና፣ በሳይንሳዊ ምርምር እና በአካባቢ ጥበቃ መስኮችም ሰፊ ፋይዳ አለው። ለአብነት የካንሰር ሕክምናን ከራዲዮቴክኖሎጂ ጋር በማያያዝ እንዲሁም ዘመናዊ የሕክምና ሥርዓቶችን በመደገፍ የጤናውን ዘርፍ ያጠናክራል።
በበሽታ እና ተባዮች ላይ ሳይንሳዊ ምርምር በማድረግ እና የፕሪሲዥን ፋርሚንግ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ከፍ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችላል።
ለኢትዮጵያ ይህ የለውጥ ጉዞ የሚጀምረው ሳይንሳዊ ዕውቀትን በመገንባት፣ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት እና ጠንካራ ተቋማትን በማቋቋም ነው።
የኢትዮጵያ የኒውክሌር ራዕይ የቴክኖሎጂ አቅምን ከልማት ጋር በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ከፍታዋን በእርግጠኛነት እውን የሚያደርግ የዘላቂ ብልጽግ አርማ ነው።
#የመደመር_መንግሥት!
#Ameco #Nuclear #Sustainable_Prosperity #FutureOfEthiopia
:- በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
