
ከቀይ ባሕር እስከ ኤደን ባሕረ ሰላጤ፣ ከንግድ እንቅስቃሴ እስከ ሰላም እና ደኅንነት፣ ከዲፕሎማሲ ግንኙነት እስከ ቀጣናዊ ኀያልነት ድረስ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ተጠቅማ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጋር ግንኙነት ታደርግ ነበር።
ከአሰብ በተጨማሪ አዱሊስ፣ ገምበዛ፣ ዘይላ እና ምጽዋ የተሰኙ የቀይ ባሕር ወደቦች እንደነበሯት የታሪክ መረጃዎች ያሳያሉ። በአክሱም ዘመን መንግሥት ኢትዮጵያ የአዱሊስ ወደብን በመጠቀም ከግሪክ እና ባዛንታይን ጋር በሰፊው ትገበያይ ነበር።
ንጉሥ አጼ ካሌብ ቀይ ባሕርን ተሻግረው የመንን እና ደቡብ አረቢያን ይቆጣጠሩ እንደነበርም ታሪክ ያስረዳል።
የአዱሊስ ወደብ አገልግሎት ሲያቆም ኢትዮጵያውያንም ምጽዋን፣ ቆይቶም በአርጎባ እና አፋር ነጋዴዎች አማካኝነት ዘይላን እና በርበራን ዋና ወደባቸው አድርገው መጠቀማቸውን ታሪክ ያሳያል።
በቅርቡ በደርግ ዘመን መንግሥት አሰብ ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያ፣ መንገዶች እና የነዳጅ ማጣሪያ ተሰርቶላት ዋና ወደብ ኾና እንደ ነበር የታሪክ መረጃዎች ያረጋግጣሉ።
ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ.ር) ” አሰብ የማን ናት” በተሰኘው መጽሐፋቸው የአሰብ ዕድገት የተረጋገጠው በኢትዮጵያ መኾኑን ገልጸዋል።
ለአሰብ ወደብ መሠረተ ልማቶች ግንባታ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን 260 ሚሊዮን ብር፣ በደርግ ዘመን 3 ቢሊዮን ዶላር፣ በኢሕአዴግ ዘመን ደግሞ ከሚሌ እስከ አሰብ ለመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ 25 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ማድረጓን በመጽሐፋቸው አስቀምጠዋል።
በዚህ የታሪክ ሂደት ውስጥ ከፊት በመሰለፍ የኢትዮጵያ ባሕር ኀይል የቀጣናውን ሰላም አጽንቷል።
በታሪክ በተፈጠረ ስህተት ግን ኢትዮጵያ የባሕር በር ተቆለፈባት፣ ባሕር ኃይሏም ተበተነ። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የባሕር በርን በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ለማግኘት ጥረት እያደረገች ነው።
የባሕር ኀይሏም ዳግም ተቋቁሟል። የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ጌትዬ ትርፌ (ዶ.ር) የቀጣናውን ሰላም እና ደኅንነት የሚያስጠብቅ፣ ገቢ እና ወጭ የንግድ ቁሳቁሶችን ደኅንነት የሚቆጣጠር የባሕር ኀይል መኾኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ታሪካዊ በሯ ልትመለስ በመኾኑ የባሕር ኀይል ማቋቋሟን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የባሕር ኀይል መቋቋሙ የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣና ሰላም እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ወሳኝነት አለውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር ኀይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ለራስ እና ለቀጣናው የሰላም ዋስትና ለመኾን ከኢትዮጵያ የበለጠ ማንም የለም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን የባሕር ኀይል ማቋቋም የምርጫ ጉዳይ አለመኾኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ባሕር ኀይል ቀይ ባሕር ላይ ወጥቶ ለራሱ እና ለቀጣናው አወንታዊ ሚናን ይወጣልም ነው ያሉት።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_08_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
