
በዓለም መድረክ ላይ ከሚካሄዱ ግዙፍ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ መድረኮች መካከል የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኮፕ አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኮፕ 32ን እ.ኤ.አ. በ2027 በመዲናችን አዲስ አበባ ታስተናግዳለች። ይህ ታሪካዊ ውሳኔ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነት፣ ተአማኒነት እና ተመራጭነት በጉልህ ያሳየ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየወሰደች ያለችው ተጨባጭ እና በተግባር የተፈተነ የመፍትሔ እርምጃ ሀገራችን ከአፍሪካ ሀገራት መካከል እንድትመረጥ እና ይህንን ዓለም አቀፍ ኀላፊነት እንድትረከብ አስችሏታል።
👉 ለመኾኑ የኢትዮጵያ የመመረጥ ሚስጥር ምንድን ነው?
የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤን ለማስተናገድ ከሚቀመጡ ዋነኛ መመዘኛዎች መካከል አስተናጋጇ ሀገር በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ያላት ቁርጠኝነት ቀዳሚው ነው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል፣ የተራቆቱ መሬቶችን እንዲያገግሙ በማድረግ፣ የደን ሽፋኗን በማሳደግ እና የታዳሽ ኀይል ልማትን በማስፋፋት ለዓለም አርዓያ የሚኾን ተጨባጭ ሥራ አከናውናለች።
ይህ በተግባር የታየ ቁርጠኝነት ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ አሳምኗል።
👉 የዲፕሎማሲ ጥንካሬ እና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ የካበተ ልምድ
አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) መቀመጫ እንደመኾኗ መጠን “የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ መዲና” የሚል ስያሜን ያተረፈች ከተማ ናት።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚካሄዱ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤዎችን ጨምሮ ሌሎች ትላልቅ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ መድረኮችን በላቀ ብቃት የመምራት እና የማስተናገድ የረጅም ጊዜ ልምድ እና ጥበብ ባለቤት ናት።
👉 ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታ እና የተሟላ የአገልግሎት አቅርቦት።
በአዲስ አበባ የተገነቡ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የሥብሠባ ማዕከላት (እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሾች እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ ባለ አምስት እና ባለ አራት ኮከብ ሆቴሎች በርካታ እንግዶችን የማስተናገድ አቅም ፈጥረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለምን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኝ ሰፊ እና አስተማማኝ የበረራ መረብ መዘርጋቱ ተመራጭ አድርጓታል፤ በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቶችና የመንገድ ትራንስፖርት መሠረተ ልማትን በማዘመን፣ ለእንግዶች ምቹ እና ቀልጣፋ እንቅስቃሴ ዋስትና ሰጥቷል።
ለዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ስኬት ወሳኝ የኾኑት የ24 ሰዓት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት፣ ፈጣን የኢንተርኔት እና የቴሌኮም ኔትወርክ እንዲሁም የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ሀገሪቱ ጉባኤውን እንድታስተናግድ ትልቅ ዕድል ፈጥሮላታል።
ከዚህም በተጨማሪ ትላልቅ ዓለም አቀፍ መሪዎች እና ሚዲያዎች የሚታደሙበትን ጉባኤ ለማካሄድ አስተማማኝ የጸጥታ እና የተረጋጋ የፖለቲካ አውድ መኖሩ ኢትዮጵያ የእንግዶችን ደኅንነት የማስጠበቅ ብቃቷን በተግባር አስመስክራለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የኮፕ 32 ጉባኤን እንድታስተናግድ መመረጧን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ውሳኔው ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና በአረንጓዴ ልማት ረገድ ለዓለም ያበረከተችው ተጨባጭ አስተዋጽኦ ዕውቅና ማግኘቱን የሚያሳይ መኾኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በታላቅ ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት ለማስተናገድ ሙሉ ዝግጁ መኾኗንም አረጋግጠዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ጉባኤ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) ውሳኔው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ተሰሚነት እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላት ተአማኒነት እያደገ ለመምጣቱ ትልቅ ማሳያ መኾኑን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ድምጽ የሚሰማባት እና ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች የሚቀረጹባት ከተማ መኾኗን በድጋሚ ያረጋገጠ ድል መኾኑንም አንስተዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_08_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
