የአሰብ ትዝታ እና የዛሬው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዞ!

6

⚓🇪🇹

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ሥልጣኔ፣ የባለቤትነት ታሪክ እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ትስስር ከጥንታዊው የአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የሀገሪቱ የሕልውና እና የዕድገት መሠረት ኾኖ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ በአዱሊስ ወደብ አማካኝነት ከሮም፣ ከቻይና፣ ከፋርስ እና ከሕንድ ጋር ሰፊ የባሕር ላይ ንግድ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደነበራት ‘ፔሪፕሉስ ኦፍ ዘ ኤሪትሪያን ሲ’ የተሰኘ የባሕር ጉዞ እና የንግድ መምሪያ መጽሐፍ አትቷል። በንግድ መርከቦቿ አማካኝነት ከሕንድ ውቅያኖስ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ እና አውሮፓ ምርቶችን በማጓጓዝ የባሕል እና የኢኮኖሚ ድልድይም ኾና አገልግላለች።

በዘመናዊው ታሪክም የቀይ ባሕር ባለቤት በነበረችበት ወቅት የአሰብ ወደብ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ አውድ የቀየረ ትልቅ ማዕከል ነበር። የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ተስፋሁን ብርሃኔ (ዶ.ር) እንደገለጹት በወቅቱ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው ድፍድፍ ነዳጅ በአሰብ ነዳጅ ማጣሪያ ተጣርቶ ቤንዚን፣ ናፍጣ፣ ኬሮሲን እና የአየር ነዳጅ ይመረትበት ነበር።

በወቅቱ ለአስፋልት እና ለፕላስቲክ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚኾኑ ተረፈ ምርቶችን በማምረት እና ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የቀይ ባሕርን ጠረፍ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ የደም ዝውውር አድርጎት ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ የባሕር ባለቤትነቷን በቅኝ ገዥዎች የጂኦፖለቲካ ካርታ ለውጥ በውጭ ኀይሎች ጫና እና በውስጥ የፖለቲካ ክፍተቶች ምክንያት ልታጣ ችላለች።

በ1983 ዓ.ም በተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ እና ኤርትራ በመገንጠሏ ምክንያት ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ ሀገር እንድትኾን መደረጉ የንግድ መርከብ ትራንዚት ወጪዋ እንዲንር በማድረግ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ለዋጋ ግሽበት እና ለደኅንነቷ ስጋት ዳርጓታል።

ግብጽ ቀይ ባሕርን የራሷ የብሔራዊ ደኅንነት እና የንግድ መሥመር ብቻ አድርጋ በመመልከት ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ደካማ አድርጎ ለማቆየት በዲፕሎማሲያዊ እና ስትራቴጂካዊ ጫናዎች ወደ ባሕር የመውጣት ዕድሏን ስታደናቅፍ ቆይታለች፤ አሁንም ቀጥላበታለች።

ኢትዮጵያ ታሪካዊ ክፍተቱን በመሙላት የቀጣናውን ሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ነፃነቷን ለማረጋገጥ እንቅስቃሴ ጀምራለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ስልጣኔ ያለ ባሕር በር ሙሉ ሊኾን እንደማይችል፣ ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ ለዘላለም ተለያይተው እንደማይኖሩ አረጋግጠዋል።

ሀገሪቱ በሰላማዊ መንገድ ወጥቶ መግቢያ በር እንድታገኝ የተሰጠው ወደ ኋላ የማይመለስ ትኩረት ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ታሪካዊ ገናናነቷ እና የባሕር ላይ ተሳትፎዋ እንድትመለስ ያግዛታል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#Ameco ​#RedSeaAccess ​​#Adulis_AssabPort #Ethiopian_History

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_07_2019_ዓ_ም

✍️ በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት