ነገ ኅዳር 8/2019 ዓ.ም ዐይኖች ሁሉ ባሕር ዳር ላይ ናቸው!

9

🌴🏟️ባለዘንባባዋ ከተማ በግዙፍ ስታዲየሟ ልትደምቅ ቀጠሮዋን ይዛለች። የካፍን ፈቃድ ያገኘው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዋሊያዎችን በሀገራቸው እንዲጫወቱ አድርጓል። ነገ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ሊያጫውት ተዘጋጅቷል።

ብሔራዊ ቡድናቸውን የናፈቁ፣ ሠንደቅ ዓላማቸውን ከፍ አድርገው ማውለብለብ የተመኙ፣ በቀለማት ደምቀው ኅብር ዜማቸውን ሊያሰሙ የናፈቁ ደጋፊዎች በቅርቡ ኢትዮጵያ ከሴኔጋል ባደረገችው ጨዋታ ድምቀትን ፈጥረው ነበር።

ከዓመታት በኋላ ዳግም ጨዋታዎችን ማስተናገድ የጀመረው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የኢትዮጵያዊያን ኩራት ኾኗል። ስታዲየሙ ነገ ማክሰኞ ኅዳር 08/2019 ዓ.ም በድጋሚ ኢትዮጵያ ከሞዛንቢክ የምታደርገውን ጨዋታ ያስተናግዳል። በሴኔጋል ጨዋታ የታየው የደጋፊ ድባብ እጅን በአፍ ያስጭን ነበር።

ፀሐይ ያልበገራቸው፣ ሙቀት ያላሸነፋቸው ደጋፊዎች ጨዋታው ከሚጀመርበት ሰዓት ቀድመው ተገኝተዋል። በሀገራቸው ሠንደቅ ዓላማ ደምቀው ታይተዋል። በኅብረ ዝማሬ የስታዲየሙን ድባብ ተዓምራዊ ማድረጋቸውም ይታወሳል።

“ውብ ሀገሬ ባንች እኮ ነው መከበሬ” የሚለው ኅብር ዜማም ነገ በደጋፊዎች ከሚሰሙ ዝማሬዎች የሚናፈቀው ነው። የቱሪዝም መዳረሻዋ ባሕር ዳር ከተማም ነገ በደጋፊዎች ትደምቃለች። የደጋፊዎች ኅብረ ድምጽ ልብን ያርዳል፣ መዳፍን በማበረታቻ ጭብጨባ ይግላል፣ ስታዲየሙ በደጋፊዎች ድባብ ይዋጣል። ዋሊያዎቹ የሚያደርጉትን ጨዋታ ደጋፊዎች ውብ ያደርጉታል ተብሎ ይጠበቃል።

ዋሊያዎቹ በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አስር 3ኛ መርሐ ግብር ከሞዛምቢክ ጋር ተጫውተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጭ 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል። በጨዋታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የማሸነፊያ ግብ 87ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ማርክነህ ከመረብ አሳርፎ ነበር።

ዋሊያዎቹ የመልስ ጨዋታቸውን ነገ በባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያደርጋሉ። ዋሊያዎቹ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ያላቸውን ዕድል ያሰፋሉ።

በምድቡ ሴኔጋል በ7 ነጥብ 1ኛ ስትኾን፣ ሞዛምቢክ በ4 ነጥብ 2ኛ፣ ኢትዮጵያ በ3 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከኢትዮጵያ በግብ ክፍያ ያነሰችው ሱዳን ደግሞ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ዋሊያዎች ማክሰኞ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም 10:00 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_07_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous article‎የኢትዮጵያ ቀጣናዊ የሰላም ቁርጥ አቋምና የቀይ ባሕር ጉዳይ
Next article‎የመገጭ ግድብ እውነታዎች