‎የኢትዮጵያ ቀጣናዊ የሰላም ቁርጥ አቋምና የቀይ ባሕር ጉዳይ

14

‎‎የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ አድማስ ሀገሪቱን ከዘመናት የጂኦፖለቲካ መገለል በማውጣት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ያላትን ስትራቴጂያዊ ቁመና ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

‎‎የዚህ የዲፕሎማሲ ጉዞ ዋነኛ ማጠንጠኛም የባሕር በር ባለቤትነትን እና አስተማማኝ ስትራቴጂያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው።

‎‎ሀገራችን ከሦሥት አሥርት ዓመታት በላይ በዘለቀው የባሕር በር እጦት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ተጋላጭ ኾና ቆይታለች።

‎‎ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ታሪካዊ እና ሉዓላዊ የነበረውን የቀይ ባሕር የባሕር በሯን የማግኘት ግልጽ ርዕይ እና ግብ ይዛ እየሠራች ትገኛለች። ይህ ጉዞም በሰላማዊ ውይይት፣ በዓለም አቀፍ ሕግ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ የመደመር ዲፕሎማሲ ውጤት ነው።

‎‎የሀገሪቱ ከፍተኛ መሪዎችም የባሕር በር ጉዳይን እንደ አንድ ወቅታዊ የፖለቲካ አጀንዳ ሳይኾን እንደ ሀገር ህልውና፣ ብሔራዊ ክብር እና የመጪው ትውልድ የብልጽግና ዋስትና አድርገው በግልጽ አስቀምጠውታል።

‎‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይኾን የህልውና ጉዳይ መኾኑን በተደጋጋሚ አስገንዝበዋል። በፍጥነት እያደገ ለሚገኘው ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እና እየሰፋ ለመጣው ኢኮኖሚ አንድ ወደብ ብቻ በቂ አለመኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸው ይታወሳል።

‎‎”ኢትዮጵያ የባሕር በር የምትፈልገው በሰላማዊ መንገድ፣ በመነጋገር፣ በመደራደር እና በጋራ ተጠቃሚነት (Give and Take) መርህ እንጂ በኀይል አይደለም” በማለት የመንግሥትን የማይናወጥ የሰላም እና የትብብር አቋምም አረጋግጠዋል። ቀይ ባሕር እና የዓባይ ወንዝ የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል የሚወስኑ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ትስስሮች መኾናቸውንም አመላክተዋል።

‎‎ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት በዓለም አቀፍ ሕግ እና በቀጣናዊ ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ የሚታይ ፍትሐዊ ጥያቄ መኾኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል። ወደብ አልባ ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስ እና የመጠቀም ተፈጥሯዊ እና ሕጋዊ መብት ያላቸው ሲኾን የኢትዮጵያ ጥረትም የአፍሪካ ቀንድን በንግድ፣ በመሠረተ ልማት እና በኢኮኖሚ በማስተሳሰር የጋራ ብልጽግናን እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ያለመ ነው ብለዋል። ይህንን ታሪካዊ ዓላማ ለማሳካትም የሁሉንም ዜጎች ብሔራዊ አንድነት እና ርብርብ እንደሚጠይቅ አሳስበዋል።

‎‎የመደመር ዲፕሎማሲ የሚያስመዘግባቸው እነዚህ ድሎች የአንድ ወቅት መንግሥት የሥራ ዘመን ስኬቶች ብቻ ተደርገው የሚታለፉ አይደሉም። ይልቁንም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ጥቅም እና ክብር በማይናወጥ ጽኑ መሠረት ላይ በማቆም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገሩ ታሪካዊ ቅርሶች ናቸው።

‎‎አማራጭ የባሕር በሮች መረጋገጥ የሀገሪቱን የገቢ እና ወጪ ንግድ ቅልጥፍና በመጨመር፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን በመቀነስ እና የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና በዓለም መድረክ በጉልህ የሚያንጸባርቁ ይኾናሉ።

‎‎#የመደመር_መንግሥት!

‎‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

‎‎#ባሕር_ዳር #ኅዳር_07_2019_ዓ_ም

‎‎ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

‎‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous articleየኢትዮጵያን ሥልጣኔ የምትፈራው ግብጽ ሴራ ሲጋለጥ!
Next articleነገ ኅዳር 8/2019 ዓ.ም ዐይኖች ሁሉ ባሕር ዳር ላይ ናቸው!