
የኢትዮጵያ ታሪክ ሲገለጥ በቀይ ባሕር እና በዓባይ ሸለቆ መሠረቱ የጣለ መኾኑን ፕሮፌሰር ላጵሶ ጌ ድሌቦ” የኢትዮጵያ ታሪካዊ መሠረቶች እና መሣሪያዎች” በተሰኘው መጽሐፍቸው አስቀምጠዋል። የዓባይ በረከትን የምትጠቀመው ግብጽም የሥልጣኔ መሠረቷን የዓባይ ወንዝ ማድረጓን መጽሐፉ ይገልጻል።
የኢትዮጵያ ሥልጣኔን የምትፈራው ግብጽ የቀጣናውን የበላይነት ለመቆጣጠር ለዘመናት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት ግጭትን ለመፍጠር ሠርታለች፤ እየሠራችም ትገኛለች።
ግብጽ የተዳከመች፣ ኋላቀር ኢትዮጵያ በዘላቂነት የማየት ፍላጎቷን እውን ለማድረግ የኢትዮጵያን የጎረቤት ሀገራት በእጅ አዙር ስትጠቀም እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። ግብጽ ኢትዮጵያ ለማዳከም ስትጥር በአጻሩ ኢትዮጵያ ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ እና በአህጉሪቱ ተሰሚነቷን ለማጉላት የመሪነት ሚና ተወጥታለች።
የማይነጥፉ የታሪክ መጽሐፍት በአጼ ቴዎድሮስ እና በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ግብጽ የሞከረቻቸው ቀጥተኛ ወረራዎች ባለመሳካታቸው በጎረቤት ሀገራት በኩል በእጅ አዙር ኢትዮጵያ ለማዳከም ለዘመናት ሥትሠራ መቆየቷን አስቀምጠዋል።
ኢትዮጵያ በውስጥ ግጭት እንድትዳከም፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የማያባራ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የትብብር ማዕቀፍ እንዳይኖራት፣ የልማት እና የኢኮኖሚ ዕድገቷ እንዳይረጋገጥ መሥራት የካይሮ መንግሥት የዲፕሎማሲያዊ የእስስት ስልት መኾኑን ዓለም ካወቀው ውሎ አድሯል። የካይሮ መንግሥት ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን እንድታጣ እና የባሕር በር እንዲቆለፉባት አድርጓል።
ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ.ር) “አሰብ የማን ናት” በተሰኘው መጽሐፋቸው አፍሪካዊ ጋዜጠኛ ግሬጉሪ ኮኘሌይ ዋቢ አድርገው” የግብጽ የአፍሪካ ቀንድ ዋነኛው ፖሊሲዋ ኢትዮጵያ በአካባቢው የበላይነት እንዳይኖራት ከቀይ ባሕር ዙርያ ማግለል ነው፤ ግብጽ ሻዕቢያን በመርዳት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትገለል አድርጋለች” በማለት በመጽሐፋቸው ገልጸዋል።
ግብጽ ይህንን የምታደርገው ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ላይ ያላት የበላይነት እና የባሕር በር መብትዋን ልታስከብር ትችላለች ከሚለው ፍራቻ በመነሳት መኾኑን በመጽሐፉ ተጠቅሷል።
አሁን ላይ ግን የግብጽ ሤራ ተበጥሷል። ኢትዮጵያ የዘመናት የካይሮን ሤራ በማክሸፍ የሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ የቀጣናው የብርሃን ምንጭ ኾናለች። ዓባይ እንዳይገደብ የክፋት ጉንጉን የዘረጋው የካይሮ መንግሥት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ፣ የመፈጸም አቅም እና ኃያልነቷን መቋቋም አቅቶት አንገት ደፍቷል።
እንደ ወርቅ ተፈትና እያደር የምትጠራው ኢትዮጵያ የካይሮን የክፋት ሤራን በየዘመኑ በተፈጠረው ትውልዷ ሠባብራለች። በጠላቶቿ ሤራ፣ በፖለቲካ እጥፋት ያጣችውን የባሕር በር ለማግኘት ጫፍ ደርሳለች። የማይቀረውን የባሕር በሯን ለመጠበቅ የባሕር ኃይልን አቋቁማ የካይሮን መንግሥት ሤራ ዛሬም በትውልዷ አክሽፋለች።
የካይሮ መንግሥት የኢትዮጵያ ጥንካሬ አስደንግጦታል፣ የክፋት ሤራዎቹ በትውልዱ ንቃት ከሽፈዋል፣ የታጠቀቻቸው ዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂዎች የካይሮ መንግሥትን አንገት አስደፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) እንኳን ሻዕቢያ፣ ግብጽ እና ሌላም ቢመጣ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አንደራደርም ብለዋል። ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን አትንኩ፣ ኢትዮጵያን አትሞክሩ አታሸንፏትም ነው ያሉት። ጥቁር አንበሳ ማሸነፍ እንጅ መሸነፍ አያውቅም ነው ያሉት። ሰላምን ማጽናት እንፈልጋለን ደፍሮ የሚሞክረን ካለ ግን ግብዓተ መሬቱን እናፋጥናለን ብለዋል።
የመደመር_መንግሥት!
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
