የጎብኝዎችን ልብ በውበቱ የሚገዛው የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ!

26

ተራራማ ሠንሠለቱ ዓይንን ይማርካል፣ ልብን ያርዳል፣ ነፋሻማው አየር ሀሴትን ይፈጥራል፣ ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድሩ ቀልብን ሰርቆ ይይዛል የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ።

ወደ ፓርኩ የሚጓዙ ጎብኝዎች በውበቱ ተማርከው፣ በሠንሠለታማ ተራሮቹ ተደምመው፣ በብርቅዬ እንስሳቱ ተደንቀው፣ ውሎ አዳራቸውን በፓርኩ ውስጥ አድርገው ለቀናት ይቆያሉ። ትዝታቸውን በካሜራቸው ቀርጸው፣ በልባቸው አትመው ይሄዳሉ።

የጎብኚዎችን ቀልብ በመግዛት የሚታወቀው አስደናቂው ፓርክ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን መገኛው ነው። ፓርኩን ከጎንደር ከተማ በስተሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 120 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከደባርቅ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተጉዘው ያገኙታል።

ፓርኩ አምስት ወረዳዎችን ያካልላል። በኢትዮጵያ ረጅሙ ራስ ደጀን ተራራን በውስጡ አቅፎ ይዟል። ከ500 ሜትር በላይ ጥልቀት ያለው እና ከከፍታ ቁልቁል የሚወረወረው ጅንባር የተፈጥሮ ፏፏቴም የፓርኩ ማራኪ ገጽታ ነው።

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዋልያ አይቤክስ፣ የምኒልክ ድኩላ፣ ቀይ ቀበሮ እና ጭላዳ ዝንጀሮ የብሔራዊ ፓርኩ ልዩ ውበት ናቸው፡፡

ፓርኩ 200 የአዕዋፍ ዝርያዎችን አቅፎ ይዟል። ወደ 2ሺህ የሚጠጉ የዕፅዋት ዝርያዎችም የፓርኩ ገጸ በረከቶች ናቸው። ሰሜን ተራራዎችን ብሔራዊ ፓርክ ይጎብኙ።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ሕዳር_06_2019_ዓ_ም

በያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየግብጽ የኋልዮሽ ዘመን ናፋቂነት እና የኢትዮጵያ የድል ጉዞ
Next articleየኢትዮጵያን ሥልጣኔ የምትፈራው ግብጽ ሴራ ሲጋለጥ!