“የሻቢያ የጥፋት ሴራ ከሽፏል፤ የኢትዮጵያ ኀያልነት ከፍታው ላይ ነው!”

52

በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘው ታሪካዊቷ እና ሉዓላዊቷ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የጅኦፖለቲካ ውጣ ውረዶች፣ የዲፕሎማሲ ፉክክሮች እና ማዕቀቦች ባየለበት፣ የዓለም የኃይል ሚዛን አሰላለፉ ኢተገማች እና ውስብስብ በኾነበት በዚህ ወቅት ብሔራዊ ጥቅሟን እና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ከመቸውም ጊዜ በበለጠ እየተጋች ትገኛለች።

በኢትዮጵያ ሰላም፣ ዕድገት እና ሉዓላዊነት ላይ የሚያነጣጥሩ የውስጥ እና የውጭ ሴራዎች አሁንም በግልጽ ይሸረቡ እንጅ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ እና በቀጣናዊ የጂኦፖለቲካ ማዕበል ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ቀጥላለች።

ሻቢያ ኢትዮጵያን ለማዳከም እና የተረጋጋች ሀገር እንዳትሆን ከጀርባ ሆኖ የሚያደርገው የጦርነት ዝግጅት እና የጥፋት ሴራ ዛሬም ቀጥሏል።

ይሁን እንጂ ይህ የሻቢያ የጥፋት አጀንዳ እና ሴራ መሬት ላይ እውን ሆኖ ኢትዮጵያን ከዕድገት ግስጋሴዋ ሊያስቆማት አልቻለም። ይልቁንም ሀገሪቱ ጠላቶቿን በማሳፈር፣ ብሔራዊ ጥቅሟን እና የቀጣናውን ጂኦፖለቲካዊ የበላይነት በፅናት እና በድል እያስከበረች ትገኛለች።

ሻቢያ ከግብጽ እና ከሀገር ውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች እና ባንዳዎች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ጦርነት ለመውጋት፣ ሰላሟን ለማናጋት እና የልማት ጉዞዋን ለማደናቀፍ ቀን ከሌት እየሠራ ቢሆንም የዚህ የጥፋት ኃይል ሴራ ከከሸፈ ሰነባብቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ማናቸውንም የውጭ ግፊት እና የጥፋት ሴራዎች በመቋቋም በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በልማት ረገድ ታአምራዊ ለውጦችን እያስመዘገበች መሆኗን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ሀገሪቱ የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች ቢበዙባትም ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷን ለማቀላጠፍ እና የቀጣናው ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን በብቃት ለማረጋገጥ እየሠራች መሆኑን በአጽንኦት መግለጻቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የውጭ እና የውስጥ ጠላት ኃይሎች የሚፈጥሩትን ማንኛውንም አደጋ በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ እና የሀገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ለመጠበቅ የሚያስችል ጽኑ መሠረትም እየጣለች ነው።

የአየር ፣ የምድር እና የባሕር ኃይሉ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች እና በስትራቴጂካዊ አቅም የተገነባ ነው።

ኢትዮጵያ በጦርነት አውድ እና በዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ብቻ ሳትወሰን በሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም ታአምራዊ ድሎችን እያስመዘገበችም ትገኛለች።

በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶች (እንደ የበጋ መስኖ ስንዴ ያሉ ልማቶች)፣ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ፣ የታዳሽ ኃይል (ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች) ልማት እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ሀገሪቱ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን የኢኮኖሚ የበላይነት ከፍ አድርጎታል።

የሻቢያ እና አጋሮቿ የጥፋት ሴራ ግስጋሴዋን ያላስቆማት ኢትዮጵያም በሰለጠነ ሠራዊት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በጠንካራ ኢኮኖሚ ራሷን አጽንታ በቀጣናው የጂኦፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን አስቀጥላለች።

#RegionalGeopolitics
#PeaceAndStability
#NationalSecurity

የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_06_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የባንዳዎች ትብብር ያልበገረው የኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ከፍታ!”
Next articleየግብጽ የኋልዮሽ ዘመን ናፋቂነት እና የኢትዮጵያ የድል ጉዞ