
ከሦሥት አሥርት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ የባሕር ኀይል ዳግም መደራጀት ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ገናናነቷ የምታደርገው ጉዞ አንዱ እና ዋነኛው ምሰሶ ነው።
የባሕር ኀይሉ ወደ ቀደመ ክብሩ መመለስ ለኢትዮጵያውያን ከወታደራዊ አደረጃጀት ባለፈ የብሔራዊ ክብር፣ የታሪክ ቀጣይነት እና የወደፊት ተስፋ መገለጫ ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ያላትን ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር፣ እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚ እና ቀጣናዊ ጆኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት የባሕር በር እና የባሕር ኀይል የህልውና እና የሉዓላዊነት መሠረቷ መኾኑን በጽኑ ታምናለች።
የባሕር በር ባለቤትነት ለኢትዮጵያዊያን የቅንጦት ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም በዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች እና በቀይ ባሕር ቀጣና ያላትን ስትራቴጂካዊ ሚና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተነደፈ የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ርዕይ አካል ነው እንጂ።
የኢፌዴሪ ባሕር ኀይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ የተቋሙን ዳግም መቋቋም እና የቀጣይ ጉዞ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ “የባሕር ኀይሉ ግንባታ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በሠለጠነ የሰው ኀይል እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በኾነ አደረጃጀት ላይ የተመሠረተ ነው”
አዲሱ የባሕር ኀይል የቀድሞውን ታሪካዊ ልምድ ከዘመኑ የባሕር ላይ ቴክኖሎጂ ጋር አጣምሮ እየተገነባ ይገኛል፤ በተለይም በባሕር ላይ ሳይንስ፣ በምሕንድስና እና በዘመናዊ የውጊያ ስልቶች የሠለጠነ ብቁ የሰው ኀይል ለማፍራት ሰፊ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
የባሕር ኀይሉ የወደፊት መዳረሻ ሀገራችን በባሕር ላይ ያላትን ደኅንነት እና ብሔራዊ ጥቅም በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቅ ነው።
ይህም የንግድ መርከቦችን ደኅንነት ከመጠበቅ ባሻገር የባሕር ላይ ዝርፊያን፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ፣ የጦር መሳሪያ እና አደንዛዥ እጽ ዝውውሮችን መከላከልን ያለመ ነው።
በተጨማሪም ከቀጣናው ሀገራት ጋር በመተባበር ለቀይ ባሕር እና ለሕንድ ውቅያኖስ ሰላም እና መረጋጋት የበኩሉን ሚና መወጣትን ያካትታል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ሕጋዊ እና ፍትሐዊ ጥያቄዋ እውን እንዲኾን እና ተልዕኮውን በብቃት ለመረከብ የሚያስችል የተሟላ ዝግጁነት እየተደረገ መኾኑን ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ አረጋግጠዋል።
ሀገሪቱ በአየር እና በምድር ያላትን አስተማማኝ የመከላከል አቅም በባሕር ላይ በማጠናከር ለመጪው ትውልድ የበለጸገች፣ የተከበረች እና በዓለም አቀፍ መድረክ ተደማጭነት ያላትን ኢትዮጵያ የማስረከብ ታላቅ ራዕይ እውን እየኾነ ይገኛል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_05_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
