
የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክት፦
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የጀመርናቸው ሥራዎች የአካባቢ ጥበቃ፣ የዘላቂ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ የደህንነትና የብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቂያ ቁልፍ ስልቶችም ናቸው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሐሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማፋጠን ለትውልድ ተሻጋሪ ብልጽግናን የማረጋገጥ ብሔራዊ ንቅናቄ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ይህንኑ ተግባራዊ ተሞክሮ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ በማስፋት በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ያላትን ተፅዕኖ እያጠናከረች ትገኛለች።
በቱርክዬ አንታሊያ የCOP31 ጉባኤ ላይ እያደረገች ባለው ንቁ ተሳትፎና በከፈተችው መካነ ርዕይ የአረንጓዴ ልማት ስኬቶቿንና ሀገራዊ ትዕምርቶቿን ለዓለም እያስተዋወቀች ነው።
በስምንት ዓመት ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኝ የተከለችው ሀገራችን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በኮሪደር ልማት፣ በበጋ መስኖ፣ በወንዝ ዳርቻ ልማት የማይበገር የኢኮኖሚ ሥርዓት እየገነባች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መሪ ሚናን ከመወጣት ባለፈ አሁን COP32ን አስተናጋጅ ሀገር ሆናለች። በኮፕ 31 ልምዷን እያጋራችና ከዝግጅቱ ልምድ እየቀሰመች እንግዶቿን በክብር ጠርታለች።
ከአንድ ዓመት በኋላ የምናስተናግደው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኢትዮጵያ የልማት ተሞክሮዋን መሬት ላይ የምታሳይበት፣ ለአየር ንብረት ፍትሕና የልማት ፋይናንስ ገቢራዊነት የምትተጋበት፣ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንትና በዓለም አቀፍ አጋርነት ያሉ ዕድሎችን የምታሰፋበት ታሪካዊ መድረክ ነው።
