‎458 ባለሀብቶችን ወደ ደብረ ታቦር ከተማ የሳበው የከተማዋ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ችግር መፈታት!

1

በደብረ ታቦር ከተማ በቂ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ባለመኖሩ በኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሠማሩ ባለሀብቶች በዘርፉ ውጤታማ ለመኾን ተቸግረው ነበር።
‎
‎ከከተማ አሥተዳደሩ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ምክንያት ባለሀብቶች ወደ ከተማ ገብተው ለማልማት እንቅፋት ፈጥሮባቸው ቆይቷል።
‎
‎የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ዋለ ዓለሙ መንግሥት የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ችግርን በጊዜያዊነት ለመፍታት በሞባይል ሰብስቴሽን አገልግሎት በዘርፉ ለተሠማሩ አልሚዎች ኀይል ሲያቀርብ መቆየቱን ገልጸዋል።
‎
‎መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በወሰደው እርምጃ ዘላቂ የኾነ የኀይል አቅርቦት ማከፋፈያ ጣቢያ በመገንባት በከተማዋ በቂ የኀይል አቅርቦት እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።
‎
‎የኀይል አቅርቦት ችግሩ መቀረፉ አልሚ ባለሀብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል ነው ያሉት። የማልማት ፍላጎት ያላቸው አልሚዎች ወደ ከተማው ገብተው እያለሙም ነው።
‎
‎ኀይልን በወረፉ ይጠቀሙ የነበሩ አልሚዎች አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ የኀይል አቅርቦት እያገኙ ነው ብለዋል። በማኑፋክቼሪንግ 97፣ በአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ 361 ባለሃብቶች በከተማዋ እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
‎
‎በማኑፋክቼሪንግ ዘርፍ 61ባለሀብቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ገብተዋል፤ 15 ባለሀብቶች ደግሞ የምርት ሂደት ላይ ናቸው ብለዋል። ወደ ሥራ ያልገቡ ባለሀብቶች ሥራ እንዲጀምሩም እየተሠራ ነው።
‎
‎መሬት ተረክበው ወደ ሥራ ያልገቡ 12 ባለሀብቶች ላይ በ2018 በጀት ዓመት በሕግ አግባብ እርምጃ በመውሰድ መሬታቸውን በመንጠቅ ለመሬት ባንክ ገቢ ተደርጓል ነው ያሉት። ለ10 ባለሀብቶች የቃል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንም ተናግረዋል።
‎
‎በ2019 በጀት ዓመት የከተማው ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ አልሚ ባለሀብቶች ወደ አካባቢው መጥተው እንዲያለሙ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። በከተማዋ የኀይል አቅርቦት ለአልሚ ባለሀብቶች ፈተና የሚኾንበት ዘመን ማብቃቱንም ገልጸዋል።
‎
‎#የመደመር_መንግሥት!
‎
‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
‎
‎#ባሕር_ዳር #ኅዳር_05_2019_ዓ_ም
‎
‎✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎ከፓን አፍሪካ እስከ ዛሬው የሰላምና የልማት ትሥሥር፦ የኢትዮጵያ አሕጉራዊ ተሰሚነት! 🌍