🇪🇹​የአፍሪካን ገጽታ የቀየረው የኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ!

7

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኀይል ዘርፍ ያስመዘገበችው ታሪካዊ ውጤት እና የአየር ንብረት ዲፕሎማሲዋ የአፍሪካ ተደራዳሪ ቡድንን ሙሉ ድጋፍ አግኝታ የኮፕ 32 ጉባኤ አዘጋጅ ኾና ተመርጣለች።

በዚህ ስኬት የአፍሪካ ግዙፉ የኀይል ማመንጫ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋነኛው አቅም ነው። ዓባይ ለዘመናት በከንቱ ከመፍሰስ ሲገደብ በረከቱ ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ አልፎ ለዓለም የተረፈ ኾኗል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል እና የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግድቡ ወደ ብሔራዊ የኀይል ማከፋፈያ መስመር በመግባቱ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት 98 በመቶ የሚሆነው ከታዳሽ የኀይል ምንጮች የሚገኝ እንዲኾን አድርጎታል።

በተጨማሪም በፕሮጀክቱ ዋና ተቋራጭ ዊቢውልድ ግሩፕ መረጃ መሠረት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን የካርቦን ልቀትን እንድትቀንስ አግዟታል።

ከዚህም በላይ ለጎረቤት ሀገራት ንጹህ ኀይል በመላክ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የአረንጓዴ ልማት ሽግግርን በግንባር ቀደምትነት እንድትመራ አስችሏታል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት አህጉሪቱን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ አቅራቢ መኾን እንደምትችልም አሳይቷል።

በተለይም ግድቡ የሚያመነጨው ንጹህ ኀይል የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመከላከል እና የቅሪተ አካል አጠቃቀምን በታዳሽ ኀይል ለመተካት የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ርብርብ በከፍተኛ ደረጃ እያገዘ መኾኑ ተመላክቷል።

ፕሮጀክቱ ከአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ጋር ተዳምሮ የካርቦን ልቀት ቅነሳን እና የአየር ንብረት መላመድን በአንድ ላይ ማቀናጀት እንደሚቻል በተግባር አረጋግጧል።

በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ዕቅድ መሠረት ሀገሪቱ የጀመረችውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሽግግር በዘላቂነት ለመደገፍም ዋነኛ ዋስትና ነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ።

ኢትዮጵያ ስኬቱን ለማስቀጠል እ.ኤ.አ እስከ 2050 በሚዘልቀው የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት እና የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የልማት ስትራቴጂ የፖሊሲ ማዕቀፍ መሠረት እየተንቀሳቀሰችም ትገኛለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የመሰሉ ግዙፍ የታዳሽ ኀይል ውጤቶች እና የተቀረጹት የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ከፍ የሚያደርጉም ናቸው።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_03_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የምግብ ሉአላዊነትን በማረጋገጥ ማህበራዊ መረጋጋትን እየፈጠረ ነው” የአዲስ አበባ አርሶ አደሮች
Next article‎የደሴ ከተማ እና አካባቢዋን የኀይል አቅርቦት በ12 እጥፍ የሚያሳድገው የኀይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል።