
አዲስአበባ: ሕዳር 03/2019 (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን በ2ኛ ዙር የስራ እድል ለተፈጠረላቸው ነዋሪዎች የግብዓት ስርጭት አካሂዷል።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በውስን የከተማ ቦታዎች ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምግብ ሉዓላዊነትን እያረጋገጠልን ይገኛል የሚሉት አርሶ አደር አበበ ገብሬ እና አሸናፊ እሸቱ ፣ ስራው የባለቤትነት ስሜትና የተረጋጋ ህይወት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ረዥምና ሕገ ወጥ የደላላ ሰንሰለትን በማሳጠር የተዘረጋው ቀጥተኛ የገበያ ትስስር የከተማዋን የዋጋ ግሽበት በመቆጣጠር ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ደግሞ የንቅናቄው ተጠቃሚ ወጣት ምህረት በለጠ ትናገራለች።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሰራተኛ እና ስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዬን ማቲዮስ፣ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች በዘርፉ ተሳትፈው የራሳቸውን ምግብ እያመረቱና ለገበያም እያቀረቡ መኾኑን ገልጸዋል።
መንግስት የተጀመሩ ስራዎች እንዳይቋረጡ የፋይናንስና የኤክስቴንሽን ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ቢሮ ሀላፊው፣ ወጣቶች ስራ ሳያማርጡ በመስራት ኢኮኖሚያቸውን እንዲያሻሽሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ በበኩላቸው፣ በሰው ተኮር ስራ የከተማ ግብርና ተጠቃሚ ቤተሰቦች ቁጥር ከ150 ሺህ ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን፣ አመታዊ የምርት መጠን ደግሞ ከ49 ሺህ ቶን ወደ 615 ሺህ ቶን ማደጉን አስታውቀዋል።
ይህንን ስትራቴጂካዊ ስራ ለማስቀጠል በ2019 በጀት ዓመት ሁለተኛ ዙር ከ800 በላይ ለኾኑ ነዋሪዎች ቄብ ዶሮዎች፣ የዶሮ መኖ እና ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
ይህ በቴክኖሎጂ የታገዘና ወጣቶችና አርሶ አደሮችን ማካተት ላይ የተመሠረተ የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ፣ አዲስ አበባን እስከ 2050 የምግብ ሉዓላዊነትን በራሷ ለማረጋገጥ የሚያስችላት ስትራቴጂ መሆኑ ተጠቁሟል።
ዘጋቢ: ኢብራሂም መሃመድ
#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ
