
አደም አብዱ በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ ፈጠራዎችን በማስተዋወቅ እና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኝ ወጣት ነው።
ሀገር በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት የአካባቢ ብክለትን የሚያስቀር እና ሰብልን ከተባይ መከላከል የሚያስችል ጸረ-ተባይ መድኃኒት ከእንቧይ ተክል በመፍጠር አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
የወጣት አደም አብዱ ዋነኛ ትኩረት ከውጭ የሚገቡ ጸረ-ተባይ ኬሚካሎችን በሀገር ውስጥ እና በተፈጥሮ ከሚገኙ ዕጽዋት በማዘጋጀት መተካት ዓላማ ያደረገ ነው።
ይህም የሀገርን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አንጻር ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳለውም ወጣት አደም አብዱ ይገልጻል።
በክልል ደረጃ በአሚኮ በኩል የአልማኮን የ “ብቁ ፈጣሪ” ውድድርን በማሸነፍ የ700 ሺህ ብር ተሸላሚ ኾኗል።
ወጣት አደም ጸረ-ተባይ መድኃኒቱ ተፈጥሮአዊ ስለኾነ ለአየር ንብረትም ኾነ በሰዎች እና በእንስሳት እንዲሁም በዕጽዋት ላይ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት የለውም ብሏል።
ምርቱ በበቂ ሁኔታ እንደሚገኝ እና በደንብ አድርጎ ተባዮችን እንደሚቀንስ ተረጋግጧል ነው ያለው።
የፈጠራ ውጤቱ አርሶ አደሩን በማገዝ ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ መረጋገጡንም ነው ያብራራው።
ሥራው በብሩህ የፈጠራ ሥራ በመወዳደር ከሥራ እና ሥልጠና ክህሎት ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ ማግኘቱንም ገልጿል።
ለሦሥት ወራት የኦንላይን ሥልጠናዎችን በመውሰድ የብቃት ማረጋገጫ እና የሥራ ማፋጠኛ ኢንቨስትመንት ሠርተፍኬት አግኝቷል።
ምርቱም በዱቄት እና በፈሳሽ መልኩ ተዘጋጅቶ ለበቆሎ፣ ለማሽላ፣ ለማንጎ፣ ለሽንኩርት፣ ለቲማቲም፣ ለስንዴ እና ለተለያዩ ጥራጥሬዎች ጥቅም ላይ በመዋል ውጤታማ መኾኑን ተናግሯል።
ወጣቱ ይህ ጸረ-ተባይ መድኃኒት ለአርሶ አደሮች በከፍተኛ ሁኔታ እገዛ እያደረገ ችግሮችን እያቃለለ መኾኑንም ነው የተናገረው።
አሁን ላይ ይህ የፈጠራ ሥራ እንደ ሀገር በሰፊው የማምረት እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን የማስቀረት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት እየተሠራ ስለመኾኑም ነው የጠቆመው።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_03_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ:- ሰመሃል ፍስሃ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
