ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራዊ ውጥኖች የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ የሚያስችሉ ናቸው።

9

በተርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ (ኮፕ 31) ጉባኤ ኢትዮጵያ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው።

የኮፕ 32 ጉባኤን ለማስተናገድ የተመረጠችው ኢትዮጵያ ከጉባኤው በርካታ ልምዶችን እያገኘች ትገኛለች።

በጉባኤው “ደኖች የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ያላቸው አስተዋጽኦ” በሚል ርዕስ በተካሄደው መድረክ ላይ፣ የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር በረከት ፍስሃፅዮን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉበት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ያስመዘገበውን ለውጥ አብራርተዋል።

ደኖች ለአየር ንብረት ጽናት፣ ለብዝኀ ሕይወት ጥበቃ፣ ለዘላቂ የኑሮ ምንጭ እና ለአረንጓዴ የሥራ ዕድል ፈጠራ ያላቸውን ወሳኝ ሚና ሚኒስትሩ አንስተዋል።

የኮፕ 32 አስተናጋጅ ሀገር እንደመኾኗም የተራቆቱ የደን መሬቶችን መልሶ ለማልማት እና እ.ኤ.አ በ2030 የደን ጭፍጨፋን ለማስቆም የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የተጠናከረ ዓለም አቀፍ አጋርነት እና ኢንቨስትመንት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት በማድረግ ዲፕሎማሲያዊ ትብብሯን ለማጠናከር፣ የኢንቨስትመንት አቅሟን ለማሳወቅ እንዲሁም በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና በታዳሽ ኀይል አቅርቦት ላይ ያላትን አቅም ለማስገንዘብ እየሠራች ነው።

በዚሁ መሠረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) እና የገንዘብ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ዋና ተደራዳሪ ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) ከዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሴክሬታሪ ኢድ ሚሊባንድ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራዊ ውጥኖችን እና የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ ያለውን አስፈላጊነት አስረድተዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሴክሬታሪ ኢድ ሚሊባንድ በበኩላቸው ሀገራቸው በዘርፉ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸው ለኮፕ 32 ጉባኤ ዝግጅቶች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾኗን አረጋግጠዋል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_03_2019_ዓ_ም

✍️ በያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየሰብል ጸረ ተባይ ኬሚካልን ከእንቧይ የሚያመርተው ወጣቱ ተመራማሪ
Next articleየሚዲያ ባለሙያዎች የሀገር ግንባታ አስተዋጽኦአቸውን እንዲያጠናክሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳሰበ።