
የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር በር እና የወደብ ባለቤትነት ጥያቄ በሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ አጀንዳዎች ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ርዕሰ ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ጉዳዩን ከታሪካዊ ዳራ፣ ከሕዝብ ቁጥር ዕድገት እና ከኢኮኖሚያዊ ህልውና አንፃር በተለያዩ መድረኮች አንስተውታል።
በሌላ በኩል ደግሞ የቀጣናው ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተንታኞች ጉዳዩን ከዓለም አቀፍ ሕግ፣ ከሉዓላዊነት እና ከቀጣናዊ መረጋጋት አኳያ የኢትዮጵያ ጥያቄ ተገቢ እንደኾነ ሲያብራሩ ይደመጣሉ።
የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተደራሽነት እና የወደብ ባለቤትነት ጉዳይ በሀገሪቱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ውይይቶች ውስጥ ዋነኛ አጀንዳ ኾኖ ቀጥሏል።
በኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ዘንድ ጉዳዩ የሀገሪቱን ታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነት የመመለስ እና የ130 ሚሊዮን ሕዝብን የኢኮኖሚ ህልውና የማረጋገጥ ጥያቄ ተደርጎ ነው የሚነሳው።
ኢትዮጵያ በጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ ዘመን ጀምሮ በቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ ጠንካራ የባሕር ላይ እንቅስቃሴ እና የንግድ መስመር እንደነበራት የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ።
በተለያዩ ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ሂደቶች በተለይም በ1983 ዓ.ም በተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ እና ኤርትራ መገንጠሏን ተከትሎ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን አጥታ ቆይታለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ይህንን ክስተት ሀገሪቱ በተፈጥሮ እና በታሪክ የነበራትን ተጠቃሚነት ያሳጣ የታሪክ እና የፖለቲካ ስህተት አድርገው ይገልጹታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በተለያዩ መድረኮች ባደረጓቸው ንግግሮች የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ሳይኾን «የህልውና ጉዳይ» መኾኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በየዓመቱ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መኾኑን ጠቅሰው ይህንን ሕዝብ ያለ ባሕር በር ህልውናውን እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቱን ማረጋገጥ እንደማይቻልም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር በ60 ኪሎ ሜትር ቅርብ ርቀት ላይ እየተገኘች እና ለአካባቢው ሰላም እና ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች ሙሉ በሙሉ ከባሕር ተጠቃሚነት መገለሏ ፍትሐዊ እንዳልኾነ አመልክተዋል።
ታዲያ ጉዳዩ በውይይት፣ በሰጥቶ መቀበል እና በጋራ ልማት መርህ ላይ ተመስርቶ መፈታት እንዳለበት ያብራራሉ።
የኢፌዴሪ ጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው የባሕር በር ጉዳይ ከሀገር ደኅንነት እና ሉዓላዊነት ጋር በቀጥታ የተቆራኘ መኾኑን ይገልጻሉ።
ፊልድ ማርሻሉ አክለውም የመከላከያ ሠራዊቱ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በየትኛውም ጊዜ ዝግጁ መኾኑን በመግለጽ የባሕር በር ጥያቄም የሀገሪቱ ቁልፍ ብሔራዊ አጀንዳ መኾኑን አረጋግጠዋል።
የባሕር ኀይል መገንባት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ ለማስጠበቅ ወሳኝ መኾኑን የገለጹት ደግሞ የባሕር ኀይል ዋና አዛዡ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ናቸው።
ተቋሙ በሰው ኀይል በሥልጠና፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በተቋማዊ አደረጃጀት ራሱን እያጠናከረ መኾኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽነት እውን ሲኾን ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም ዋና አዛዡ አብራርተዋል።
በአጠቃላይ በቀይ ባሕር 1ሺህ ኪሎ ሜትር ወሰን የምትጋራው ኢትዮጵያ የዜጎቿን ህልውና ለማረጋገጥ እና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እና በአንጡራ ሀብቷ ዳር ላይ ኾና የበይ ተመልካች ላለመኾን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ እየተጋች ትገኛለች።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_03_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
