
”ኢትዮጵያን ማንም በኀይል ሊወራት አይችልም። ለመመከት የሚያስችል በቂ አቅም አለን፣ ጀግኖች ነን! ማንንም አንነካም፤ ከነኩን ግን ለማንም አንመለስም” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ንግግር የኢትዮጵያን የዘመናት የሉዓላዊነት ጽናት፣ ብሔራዊ ኩራት እና ወታደራዊ አቅም አጉልቶ የሚያሳይ ነው።
መልዕክቱ የሀገሪቱን የታሪክ አደራ ከተጨባጭ የዛሬ አቅም ጋር በማስተሳሰር ለወዳጅ የሰላም በሯ ክፍት መኾኑን፣ ለጠላት ደግሞ የማያዳግም የማስጠንቀቂያ ደወል ነው።
በረጅም ዘመን ታሪኳ የትኛውንም ሀገር አስቀድማ አጥቅታ የማታውቀው ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን የደፈረን ጠላት ግን አሳፍራ ከመመለስ ወደ ኋላ ብላ አታውቅም።
በሰላም አብሮ መኖርን ለሚሹ ወዳጆች የጸጥታ ዋስትና የሚሰጠው ይህ አቋም የሀገሪቱን ሰላም ለማናጋት ለሚቋምጡ የውጭ ኀይሎች የኢትዮጵያን መሬት መርገጥ እሳት እንደመጨበጥ የሚቆጠርበትን ታሪካዊ እውነታም ያስታውሳል።
እውነተኛ ሉዓላዊነት በጦር ሜዳ ጀግንነት ብቻ ሳይኾን ራስን በቴክኖሎጂ እና በምርምር በማብቃት የሚረጋገጥ ነው።
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ስንገዛ የነበርናቸውን ማምረት ጀምረናል” በማለት ሀገሪቱ በወታደራዊ ቴክኖሎጂ እና በአምራች ዘርፍ ያደረገችውን አስደናቂ ሽግግር የገለጹት።
በውጊያ የታዩ ክፍተቶችን ሞልቶ የራስን መሣሪያ ማምረት መቻል ኢትዮጵያ ከየትኛውም የውጭ ጫና፣ የጦር መሣሪያ እገዳ እና ከተጽዕኖ ፈጣሪዎች ማዕቀብ ነጻ እየኾነች መምጣቷን የሚያበስር ነው።
በአጼ ምኒልክ ዘመን ዜጎች ያለ ዘመናዊ ትጥቅ እና በባዶ እግራቸው የዓለምን ኀያላን በዓድዋ ምድር በመምታት መላው ጥቁር ሕዝብን ነጻ አድርገዋል።
የዛሬዋ 130 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት፣ ዘመናዊ ወታደራዊ አቅሟን ያፈረጠመች እና ያው የጀግንነት ደም በሥሯ የሚንተከተክ ሀገር ፈጽሞ የማትደፈር የብረት አጥር መኾኗን በድጋሚ እያሳየች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የትኛውንም ስጋት እና ፈተና በድል ለመቀልበስ የሚያስችል የማይበገር ሀገራዊ አንድነት እና የጽናት ወኔ አላት። ይህም ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣን አካል በአንድነት አሳፍሮ የሚመልስ የማይናወጥ ጀግና ሕዝብ እንዳላት ያሳያል።
ኢትዮጵያ በትላንት ታሪኳ ብቻ ሳትኮፈስ ከትላንት ተምራ የዛሬ አቅሟን በአስተማማኝ መሠረት ላይ የገነባች ሉዓላዊት ሀገር መኾኗን በይፋ አውጃለች።
ይህም ዜጎቿ በኩራት እና በጥልቅ የደኅንነት ስሜት ቀና ብለው እንዲራመዱ የሚያደርግ፣ ለዓለም ደግሞ የኢትዮጵያን የማይነቃነቅ የህልውና ጽናት የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#Ameco #SpiritOfAdwa #ENDF #UnbreakableEthiopia
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_03_2019_ዓ_ም
✍️:- በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
