“ጠላቶች ያወራሉ፤ ኢትዮጵያ ግን በጽናት ትገነባለች”

4

ለበርካታ ዓመታት ፕሮጄክትን ገንብቶ ማጠናቀቅ የኢትዮጵያ ፈተና ነበር። ግንባታቸው ተቋርጦ ዓመታትን በባይተዋር መንገድ የቆሙ መሠረተ ልማቶችን በየቦታው መመልከትም አዲስ አልነበረም።

ከመንገድ እስከ ግድብ፣ ከትምህርት እስከ ጤና ተቋማት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ድረስ ሲጀመሩ እንጂ ሲጠናቀቁ ማየት የተለመደ አልነበረም።

የሕዝብ ሃብት ፈስሶባቸው ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጄክቶች ማኅበረሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጫና ሲፈጥሩ ቆይተዋል።

አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ ጀምራ መጨረስን፣ አቅዳ መፈጸምን፣ ተግብራ ማሳየትን ባሕል አድርጋለች። መንግሥት በተቋማት ላይ ባደረገው ሪፎርም ለዓመታት ተጓትተው የኢኮኖሚ ጫና ሲፈጥሩ የነበሩ ፕሮጄክቶች እየተጠናቀቁ ይገኛሉ።

ከሕዳሴ እስከ መገጭ ግድብ፣ ከአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ እስከ ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ እና ሌሎች በርካታ የልማት ፕሮጄክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።

የሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ይፋ ያደረጓቸው የጉባ ብሥራት ፕሮጄክቶች ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የመሠረተ ልማት ለውጥ ለማስመዝገብ እየሠራች መኾኑን ያመላክታሉ።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ፣ የጎዴ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ፣ የጎዴ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ፣ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤት ልማት ፕሮጄክቶች ወደ ሥራ መግባት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትንሣኤ የሚያበሥሩ እንደሚኾኑ ታምኖባቸዋል።

በገጠር እና በከተማ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የኢኮ ሪዞርት ግንባታዎች፣ የሀገር ውስጥ የአየር መንገድ መዳረሻ ማስፋፊያዎች፣ የውኃ ግድብ ፕሮጄክቶች የኢትዮጵያን የመፈጸም አቅም እያረጋገጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ የዝመና፣ የለውጥ እና ራሷን የመቻል ጉዞ መጀመሩን መግለጻቸው ይታወሳል። መሠረተ ልማቶችን ጀምሮ አለመጨረስ ጥፋት መኾኑንም ተናግረዋል።

በየቦታው ተቀምጠው ያልተጠናቀቁ ፕሮጄክቶች የተበራከቱት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅሞች ወደ አቅም የመቀየር ልምምዷ ውስን በመኾኑ ነው ማለታቸውም ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ባላት አቅም ጀምራ መጨረስ እና መከወን እንደምትችል ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ከውኖ ያለመጨረስ ስብራት ኢትዮጵያን የጎዳ በመኾኑ መቀየር አለበት ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን እንጀምራለን፣ በትጋት እንሠራለን፣ እንጨርሳለን ነው ያሉት። እነሱ ያወራሉ እኛ እንሠራለን፤ በሥራዎቻችንም ኢትዮጵያን ከፍ እናደርጋለን ነው ያሉት።

የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_02_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሥራ የሚፈጠርላቸውን ወጣቶች ገንዘብ ከመያዛቸው በፊት ዕውቀት እንዲጨብጡ ማድረግ ይገባል።
Next articleየረጅም ጊዜ አብሮ የመሥራት ግንኙነትን ማስቀጠል ይገባል።