
ከስደት ተመላሽ ወጣቶች የክህሎት ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሥራና ክህሎት መምሪያ ገልጿል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሙሉ ደሳለኝ ባለፉት ዓመታት ወጣቶችን ከኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት እና ከጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበር የክህሎት ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በከተማዋ ለሚገኙ ከ56ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል።
የከተማዋን ወጣቶች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ምክትል ኀላፊዋ በተለይም ተፈናቃዮች እና ከስደት ተመላሻ ወጣቶችን ለማበረታታት ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የተሻላ ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑንም ተናግረዋል።
የጎንደር ቀጣና ኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲቲዩት አስተባባሪ ብርሃኑ አየለ ባለፉት ዓመታት በጎንደር እና አካባቢው ከ100ሺህ በላይ ወጣቶች እና ከስደት ተመላሾች የተለያዩ የሙያ ክህሎት ሥልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል። 4ሺህ ለሚኾኑት ብድር በማመቻቸት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም አብራርተዋል።
ሥልጠናው ቀጣይነት ያለው ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ ወጣቶች ገንዘብ ከመያዛቸው በፊት ዕውቀታቸውን ማሳደግ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ከስደት ተመላሽ የክህሎት ሠልጣኞቹ መካከል አንዷ የኾነችው ወጣት ሰብለ ጌጡ በአረብ ሀገራት ባሳለፈችባቸው ዓመታት በርካታ ፈተናዎችን ማየቷን አስታውሳለች። በሀገሯ ሠርታ ለመለወጥ ቁርጠኛ መኾኗን ተናግራለች።
ወጣት ከድር ጀማል በሥልጠና ያገኘውን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የኢኮኖሚ አቅሙን ለማጠናከር ዝግጁ መኾኑን ገልጿል።
ኢትዮጵያ የብዙ ጸጋ ባለቤት ናት ያሉት ሠልጣኞቹ ያለውን እምቅ ሀብት በመጠቀም ለመለወጥ ዝግጁ እንደኾኑም ጠቁመዋል።
የሚሰጣቸው ሥልጠና ለሚሠሩት ሥራ መነሻ እና ስኬታማ መኾን የሚያስችላቸው መኾኑንም አንስተዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ጎንደር #ኅዳር_02_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ደስታ ካሳ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
