🌾 በአማራ ክልል ከ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ይጠበቃል።

4

በአማራ ክልል ከሚመረቱ ሰብሎች መካከል “ነጭ ወርቅ” በመባል የሚታወቀው የሰሊጥ ምርት አንዱ ነው። ምርቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ምርቶች መካከልም የሚጠቀስ ነው።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) በበጀት ዓመቱ ከ519 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል።

ከ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የምርት መሠብሠብ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ነው። እስካሁን ከ315 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መሠብሠቡን አንስተዋል።

ሰሊጥ በክልሉ በብዛት በቆላማ አካባቢዎች የሚመረት እና ዋና ከሚባሉ የቅባትና የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ ሰብሎች አንዱ በመኾኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት። ሰብሉ በወቅቱ እንዲሠበሠብ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። የተሻለ ምርት ይጠበቃል ነው ያሉት።

የሰሊጥ ምርቱ በቀላሉ ለብክነት የሚዳረግ በመኾኑ በጥንቃቄ እንዲሠበሠብ እና እንዲከማች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋት ሥራ መከናወኑን ነው የገለጹት። በተለይም ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና በሌሎችም ጉዳት እንዳይደርስበት በጥራት ለመሠብሠብ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች እና ባለሀብቶች የሀብት ምንጭ በመኾን የሀገርን ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል። እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ ለመላክ እየተሠራ እንደኾነ ነው የተናገሩት። በሀገር ውስጥ ሰሊጥን እንደ ግብዓት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች እየተገነቡ መኾናቸውንም አብራርተዋል።

የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_02_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከምድር እስከ ሰማይ፤ ከባሕር እስከ ሳይበር የነገሠው የኢትዮጵያ አለኝታ!
Next articleሥራ የሚፈጠርላቸውን ወጣቶች ገንዘብ ከመያዛቸው በፊት ዕውቀት እንዲጨብጡ ማድረግ ይገባል።