
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የቱርክዬ መንግሥት እና ሕዝብ ላደረጉልን ደማቅ አቀባበል፣ ድርድሩን ለምትመራው አውስትራሊያ የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት እርምጃ፤ የዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ ለማሻሻል፣ የመቋቋም አቅምን ለማጠናከር እና የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን ዘላቂ ለማድረግ እጅግ ወሳኝ የኾነ የኢኮኖሚ ፖሊሲያችን አካል ነው። በመደመር ፍልስፍናችን እየተመራን፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብራችን እስካሁን ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ችለናል ነው ያሉት። በተመሳሳይ መልኩ የታዳሽ ኃይል ልማትን፣ ዘላቂ የከተማ ግንባታን እና የአየር ንብረት ተስማሚ መፍትሔዎችን በስፋት እያሳደግን እንገኛለን ብለዋል።
አሁን ላይ ከቃል ኪዳን ባለፈ ወደ ፈጣን ተግባራዊ እርምጃዎች መሸጋገር ይኖርብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም በቀላሉ ሊገኝ በሚችል የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ ይበልጥ ጠንካራ በኾኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች እና ተጋላጭ ለኾኑ ማኅበረሰቦች የመቋቋም አቅም ግንባታ ላይ በሚደረግ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ተግባራዊ መደረግ አለበት ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ መጪውን የCOP32 ፕሬዝዳንትነት ስትረከብ እነዚህን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በግንባር ቀደምትነት እንደምታራምድ ገልጸዋል። ስኬታማ ውጤት እንዲመዘገብም ከCOP31 ፕሬዝዳንት ጋር በቅርበት እና በትብብር ትሠራለች ብለዋል። መላውን ዓለም ለCOP32 ጉባኤ ምድረ ቀደምት ሀገር ወደኾነችው ኢትዮጵያ ለመቀበል ዝግጁ ነን ነው ያሉት።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
