
ባሕር ኃይል ለአንድ ሀገር ብሔራዊ ደኅንነት፣ ብሔራዊ ጥቅም እና ኢኮኖሚያዊ እድገት መሠረታዊ ነገር ነው። ኢትዮጵያም ቀደም ባሉት በርካታ ዓመታት ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ገናና የባሕር ኃይል የነበራት ባለ ታሪክ ሀገር ናት። ይህም ከባሕር በር ባለቤትነቷ ጋር የተሳሰረ ነው።
ነገር ግን በቀደመው ሥርዓት በተሠራው ሴራ ምክንያት የባሕር በሯን እንድታጣ፤ የባሕር ኃይሏም እንዲበተን ተደርጓል። ይህም ኢትዮጵያ በታሪኳ ከገጠሟት መጥፎ የታሪክ አጋጣሚዎች እና ስብራቶች መካከል አንዱ ኾኖ ተመዝግቧል።
ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ ሀቋን ተነጥቃ፣ መብቷን አጥታ፣ ከርስቷ ተነጥላ፣ የባሕር በር ተዘግቶባት ከ3ዐ ዓመታት በላይ በደኅንነት ስጋት ቆይታለች። በአሁኑ ወቅት የባሕር ኃይሏን መልሶ በመገንባት የኢትዮጵያን የቀደመ ክብር ለመመለስ ስትራቴጅ ተነድፎ ወደ ተግባር ተገብቷል።
የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የባሕር በር ጥያቄ የሚመለሰው በጠንካራ የባሕር ኃይል ነው ብለዋል። በግፍ ያጣችውን የባሕር በር ለማስመለስም ኢትዮጵያ ጠንካራ የባሕር ኃይል የገነባች መኾኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር ትስስር ለሺህ ዘመናት የቆዬ፣ ለሺህ ዘመናት የንግድ ልውውጥ ያደረገችበት እና ከዓለም ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ግንኙነቷን ስታሳልጥበት የኖረችበት መኾኑን ያስረዳሉ። ኢትዮጵያውያንም ሕይወታቸውን ሰውተው ዋጋ ከፍለውበታል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ስታቋቁም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የባሕር በር ጉዳይን ሲያነሳ ያለ አግባብ ያጣነው ሀቃችን ስለኾነ ነው ብለዋል። “ባሕር ተዘግቶብን፣ ሀቃችንን አጥተን፣ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት አሻግረን እያየን የደኅንነት ዋስትና አጥተን መኖር የለብንም” ነው ያሉት።
ጥያቄያችን ግልጽ ነው የሚሉት ዋና አዛዡ ሕጋዊ ባልኾነ መንገድ ያጣነውን የባሕር በር በሕግ እና በዲፕሎማሲ እስከ መጨረሻው ድረስ ሄዶ ማስመለስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
“ቀይ ባሕርን ወደ ቀደመ ግዛት ሀገሩ በማስመለስ የኢትዮጵያን ትንሣኤ ማረጋገጥ የግድ ይላል” ነው ያሉት። ይህንን አስበንም እየተዘጋጀን ነው ብለዋል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ወደ ቀይ ባሕር መመለሱ የማይቀር መኾኑንም አረጋግጠዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
