
ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት የሚካሄደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ ታስተናግዳለች።
ዛሬ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ የዘመናችን ትልቁ ፈተና ነው። የአየር ንብረት ለውጡን ለመቋቋም 198 ሀገራት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር ኾነው በየዓመቱ እየመከሩ ይገኛሉ።
የዘንድሮው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ31) በቱርክ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ቀርጻ ወደ ሥራ መግባቷ እና አርዓያነት ያለው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቷ የኮፕ 32 ጉባኤን እንድታስተናግድ ዕድል ፈጥሮላታል።
ላለፉት 30 ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ሥርዓት ጉባኤ ተሳታፊ የነበረችው ኢትዮጵያ ይህንን ጉባኤ በማስተናገድ ደረጃዋን ከቀጥታ ተሳታፊነት ወደ አጀንዳ ቀራጭነት ከፍ አድርጋለች።
ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የፊት መስመር እንድትሰለፍ እና በአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ የሚያጎላ ስኬት ነው።
ለመኾኑ ኢትዮጵያ 32ኛውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት (ኮፕ32) ጉባኤ ማስተናገዷ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳው ምንድን ነው?
የመጀመሪያው ብዙ ቁጥር ያላቸው ዓለም አቀፍ ተሳታፊዎች እና እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እንግዶቿ የምግብ፣ የመጠጥ፣ የሆቴል እና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን በመጠቀማቸው ላገኙት አገልግሎት ክፍያ ይፈጽማሉ።
ይህም ኢኮኖሚውን የሚደግፍ የውጭ ምንዛሬ እንዲፈጠር ያስችላል፤ ይህ ደግሞ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርትን (GDP) ከፍ ለማድረግ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ሌላኛው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ተሳታፊዎች ከጉባኤው ጎን ለጎን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለመጎብኘት ዕድል ያገኛሉ፤ ይህም የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ያነቃቃዋል።
ጉባኤው የሀገሪቱን የንግድ እና የኢንቨስትመንት አቅም ለዓለም የሚያሳይ ትልቅ ዕድልም ይፈጥራል።
እንግዶች የኢትዮጵያን እውነተኛ አቅም በአካል በመመልከት በሀገሪቱ ላይ የኢንቨስትመንት ፍላጎት እንዲያዳብር እና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ያደርጋል።
ዓለም አቀፍ እንግዶች ጥራት ያላቸው አገልግሎቶች እና መሠረተ ልማቶች ስለሚፈልጉ፣ መንግሥት መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት እና በማሻሻል ረገድ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል፤ ይህም ለሕዝቡ የረጅም ጊዜ ዘላቂ ጥቅም ይሰጣል።
ዳፕሎማሲያዊ ጠቀሜታው
ጉባኤው አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኝባት መኾኗን በማጠናከር፣ በምሥራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ይበልጥ ያጎለብታል።
ጉኤው የአፍሪካን ልዩ ችግሮች በተለይም እንደ የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ የጉዳት እና ማካካሻ ፈንድ ያሉ ጉዳዮችን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ በስፋት ለማንጸባረቅ እና የዲፕሎማሲ ብቃቷን ለማሳየት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) እንደገለጹት ኢትዮጵያ አዲስ አበባ በምታካሂደው የኮፕ 32 ጉባኤ በአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ እና በዘላቂ ልማት ያላትን ልምድ እና ተሞክሮ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ታካፍላለች ብለዋል። በጉባኤው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ዓለማቀፋዊ ትብብርን ለማጠናከር ያስችላታል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ እና ሌሎች ታዳጊ ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ጉዳዮች ድምጽ በመኾንም ታሰማለች ነው ያሉት።
የገንዘብ ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ.ር) ኮፕ 32 የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስፋት፣ ለአየር ንብረት ጽኑ ልማት አስፈላጊ የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት፣ የአፍሪካ የአየር ንብረት አጀንዳን ሊደግፉ የሚችሉ አጋርነቶችን ለማጠናከር ወሳኝ መኾኑንም ጠቁመዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
