
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የአየር ንብረት መቋቋሚያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት እና በዓለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ በጽኑ ታምናለች።
ኢትዮጵያ በበካይ ጋዝ ልቀት እጅግ አነስተኛ ድርሻ ያላት ቢኾንም በአየር ንብረት ለውጥ ግን ተጋላጭነቷ ከፍተኛ ነው። እንደ Our World in Data፣ Climate Change Tracker እና NAP global network ያሉ የካርበን መከታተያዎች እ.ኤ.አ በ2025 ያወጡት መረጃ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዓመታዊ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ከዓለም አቀፉ ልቀት 0.04 በመቶ ብቻ ነው።
በአንጻሩ በአሜሪካ ኖትር ዳም ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ተጋላጭነት መመዘኛ ማዕክል መረጃ ሀገሪቱ በተጋላጭነት ደረጃ 155ኛ ላይ ትገኛለች። ይህ ከፍተኛ ተጋላጭነት ፈጣን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እና የፋይናንስ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልጋት ያሳያል።
ለዚህም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል መፍትሔ ሰጪ ሀገር መኾኗን በተግባር አሳይታለች። ከዚህ በተጨማሪ የምታመነጨው ከ90 በመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ኀይል ከውኃ፣ ከንፋስ እና ከጂኦተርማል የሚገኝ በመኾኑ በአረንጓዴ ልማት ረገድ ለታዳጊ ሀገራት እውነተኛ አርዓያ መኾን ችላለች።
እነዚህ የአየር ንብረት ለውጥን ለመጋፈጥ የወሰደቻቸው የዋና ተዋናኝነት ሚናዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ዓለም አቀፍ ጉባኤን (COP32) ወደ አዲስ አበባ ለመሳብ ዕድል ፈጥሮላታል።
ቁጣራቸው የበዛ የዓለም ሀገራት መሪዎች፣ የምሁራን እና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች የሚሳተፉበት COP 32 እ.ኤ.አ በ2027 መገባደጃ በኢትዮጵያ ይካሄዳል።
በታላቁ መድረክም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ካሉ ታዳሽ የኀይል ምንጮች የምታመነጨውን ንጹሕ የኤሌክትሪክ ኀይል የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮዋን ለዓለም ታሳያለች።
የኮሎምቢያ ዘላቂ ኢንቨስትመንት ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪዎች The Conversation በተሰኘ የመገናኛ ብዙኅን ላይ ባሳተሙት ጽሑፍ ኢትዮጵያ የምታስተናግደው COP 32 አፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ስብሰባ እንድታስተናግድ እድል እንደሚሰጣት ጽፈዋል።
ባለሙያዎቹ አፍሪካ ከCOP 32 በፊት የተቀናጁ ቀጣናዊ የኀይል ሥርዓቶችን የመገንባት፣ የካፒታል ወጪን የመቀነስ፣ የመቋቋም አቅም ያላቸውን የምግብ ሥርዓቶች በገንዘብ የመደገፍ እና ተፈጥሮን ወደነበረበት የመመለስ ሥራዎቿን ማጠናከር ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባት መክረዋል። ይህንንም ኢትዮጵያ ቀድማ ተግባራዊ አድርጋዋለች።
አህጉሪቱ እቅዶቿን አዘጋጅታ እና የተወሰኑ ማሻሻያዎችን አስቀድማ ወደ COP 32 መድረክ ካመጣች ኢትዮጵያ በዘርፉ ለሠራቻቸው ተግባራት ዕውቅና፣ የፋይናንስ እና የሥራ ዕድልን የማስፋት ትልቅ ምዕራፍ ይኾናታል ብለዋል።
የኮፕ 32 አዘጋጇ ኢትዮጵያ ለመድረኩ ከአሁኑ ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት ውስጥ ገብታለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስን (ዶ.ር) የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት አድርጋ በመሾምም የዲፕሎማሲ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች። አፍሪካ በአንድ የተቀናጀ የጋራ አቋም እንድትቀርብም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመተባበር የቀጣናዊ ድርድር ሥራዎችን በግንባር ቀደምትነት እየመራች ነው።
ሀገሪቱ በዚህ ታሪካዊ መድረክ የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮዋን በማጋራት ለተፈጥሮ ጥበቃ የሚውል ዓለም አቀፍ ፈንድ ለማሠባሠብ፤ በልማት ባንኮች በኩል የመላመድ ፋይናንስ እንዲለቀቅ፤ እንደ አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት የታዳጊ ሀገራትን የብድር ወለድ እና የአደጋ ግምገማ መለኪያዎች እንዲያሻሽሉ ግፊት ለማድረግ፣ በግድቧ የምታመነጨውን ኀይል ለጎረቤቶቿ በማጋራት ተግባራዊ የተቀናጀ ቀጣናዊ የኀይል ሥርዓቷን ለዓለም የምታሳይበት ወሳኝ አጋጣሚ እንደሚኾንም ይጠበቃል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#Ameco #COP32 #ClimateAction #Ethiopia
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ !
