
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከታሪካዊ የፍትሕ እጦት እና ከጂኦፖለቲካዊ ፍላጎት አልፎ ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀይ ባሕር አካባቢ እየተፈጠሩ ባሉ ተለዋዋጭ እውነታዎች የተደገፈ የሕልውና፣ የኢኮኖሚ እድገት እና የቀጣናው ሰላም የማዕዘን ድንጋይ ኾኗል።
ከአፍሪካ ቀንድ እምብርት ኾነው ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዞ ያለባሕር በር መኖር የኢኮኖሚ አንገት ማነቆ ብቻ አይደለም፤ የተፈጥሮን ሕግ እና የታሪክ ፍትሕን መቃረን ጭምር እንጂ። ኢትዮጵያ የባሕር በር ስትጠይቅ በሌሎች ላይ ኪሳራን ለማድረስ ሳይኾን የራሷን የልማት እና የደኅንነት መብት ለማስከበር ነው።
ቀይ ባሕር ዛሬ የዓለም የንግድ መስመሮች ማዕከል፣ የኃይል አቅርቦት አንጓ እና የዓለም አቀፍ ፉክክር ዋነኛ መድረክ ነው። በዚህ የባሕር ክልል ውስጥ መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የንግድ እንቅስቃሴ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል፣ የሽብርተኝነት እና የባሕር ላይ ወንበዴዎች ሥጋት እንዲቀረፍ ኀላፊነት የሚሰማው ታማኝ አጋር ኃያል ያስፈልጋል።
የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፋም በምሥራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲካ ላይ ባደረጉት ጥናት የአንድ ሀገር ብሔራዊ ደኅንነት እና ነጻ የውጭ ፖለቲካ መሠረቱ የራሱ ነጻ የባሕር በር መኖር ነው ሲሉ ተንትነዋል።
የሥራ አመራር አማካሪው እና ፖለቲከኛው ጌትዬ ትርፌ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከታሪካዊ የሉዓላዊነት እና የኢኮኖሚ መብት አልፎ ቀይ ባሕር ራሱ ለሰላም እና መረጋጋት ሲል ኢትዮጵያን እየፈለገ ነው ይላሉ።
በቀጣናው የውጭ ኃይሎች ሴራ እና አለመረጋጋት እየፈተነ ባለበት ሁኔታ የዓለምን የንግድ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስኬድ የኢትዮጵያ ተሳትፎ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መግባት ጥያቄ የሁለትዮሽ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የቀይ ባሕርን ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ ቀጣናዊ ውሕደትን ለማፋጠን፣ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር እና ለሁሉም የጠረፍ ሀገራት የጋራ ዕድገት ወሳኝ ታሪካዊ እና ጂኦስትራቴጂካዊ መፍትሔም ጭምር ነው።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
