ከዝቅተኛ አምራችነት ወደ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት- የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ጉዞ!

4
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ ተግባራዊ የተደረጉ አዳዲስ ለውጦች በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገቡ ነው። ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የነበሩ ጥብቅ እና አግላይ የሕግ ገደቦች፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረቶች፣ የተንዛዛ ቢሮክራሲ፣ የኤሌክትሪክ ኀይል ተደራሽነት፣ የመሬት አቅርቦት እና ሌሎች ክፍተቶች የሀገር ውስጥ እና የውጭ አልሚዎችን ይፈታተኑ ነበር።
ከለውጡ ወዲህ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ በተወሰዱ እርምጃዎች ማንኛውም የውጭ አልሚ በተለያዩ ዘርፎች መሳተፍ የሚያስችለውን አሠራር መተግበር ተችሏል። የካፒታል ገበያ ሕግ መውጣት፣ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ አገልግሎት አሠጣጥ በዲጂታል መንገድ መደራጀቱ፣ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በስፋት እንዲገቡ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የንግድ መስኮች ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መደረጋቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ውድድር እንዲፈጠር እያደረገም ነው። ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፖሊሲን በማጽደቅ ከወቅታዊ የኢኮኖሚ ኹኔታዎች እና ከዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ጋር እኩል ለመራመድ እየሠራች ነው። ፖሊሲው የግሉ ዘርፍ የአምራች ኢንዱስትሪው ዋነኛ አንቀሳቃሽ እንዲኾንም ዕድል ፈጥሯል።
ምቹ የንግድ ሥነ-ምኅዳር በመፍጠር፣ የመሬት እና የማምረቻ ቦታ አቅርቦትን በማሻሻል፣ አሥተማማኝ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦትን በማሳደግ፣ የፋይናንስ ሥርዓቱን በማዘመን፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየተሠራ መኾኑን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ለኢንቨስትመንት መነቃቃት ደግሞ ኢትዮጵያ የኮፕ 32 (COP 32) ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤን ማስተናገዷ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ሁኔታ ለመሳብ እና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ገጽታ ለመቀየር ትልቅ ዕድልን ይፈጥራል።
የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት መዳረሻነትን ለማሳወቅ፣ በታዳሽ ኀይል ያላትን አቅም ለማሳየት፣ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር የንግድ ትሥሥር ለመፍጠር፣ ለባለሃብቶች ምቹ እና ተስማሚ የኢንቨስትመንት ሃብት መኖሩን ለማሳየት ያግዛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ያካሄደችው የኢኮኖሚ ሪፎርም ዕድገቷ እንዲረጋገጥ፣ የዓመታት የኢኮኖሚ ሥብራቷ እንዲቃና አድርጓል ብለዋል። ችግሮችን በመቅረፍ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ወደ 67 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።
በዘርፉ በትኩረት በመሠራቱ በማዕድን ሀብት 24 በመቶ፣ በማኑፋክቼሪንግ 20 ነጥብ 3 በመቶ፣ በኀይል አቅርቦት ደግሞ 23 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት። የውጭ ባለሃብቶችንም ለመሳብ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑንም ተናግረዋል።
✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“በአነስተኛ ካፒታል የተጀመሩ ኢንቨስትመንቶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ የካፒታል አቅማቸውን ማሳደግ ተችሏል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየወባ በሽታ እየፈተናት ያለችው ባሕር ዳር!