የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ተስፋ ሰጪ ሥራዎች- ከድንች እስከ ነጭ ወርቅ ምርታማነት

7
በአማራ ክልል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ከተቋቋሙት የምርምር ተቋማት መካከል የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል አንዱ ነው። ማዕከሉ ከፎገራ እስከ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን፣ ከበለሳ እስከ አርማጭሆ እና መተማ የሚዘልቀውን ሠፊ የጎንደር ቀጣና ለመደገፍ ታሳቢ የተደረገ ነው።
የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ ተስፋዬ (ዶ.ር) ለአሚኮ እንደተናገሩት ማዕከሉ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በምርምር የማውጣት፣ የማስተዋወቅ፣ የማላመድ፣ የመነሻ ዘር ማባዛት እና ወደ ምርት የማስገባት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
ሥራ አስኪያጁ ማዕከሉ ከደጋማው እስከ ቆላማው አካባቢዎች የሚላመዱ እና የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር በመልቀቅ ወደ ምርት እንዲገቡ ማድረጉን ይገልጻሉ። በደጋ አካባቢዎች ባቄላ፣ አተር፣ ስንዴ፣ ምስር፣ ድንች፣ የምግብ እና የቢራ ገብስ ዝርያዎችን በስፋት ማሠራጨቱን አብራርተዋል።
ለአብነትም ማዕከሉ የተለያዩ የባቄላ ዝርያዎችን፣ “ፉሪ” የተባለ የምስር ዝርያ እንዲኹም “በለጠ” የሚባለውን የድንች ዝርያ በምርምር በማውጣት እና በማሠራጨት በደባርቅ እና ዳባት አካባቢዎች በስፋት የተሻለ ምርት እንዲሰጡ ስለማድረጉ አንስተዋል።
በወይና ደጋ በተለይም በበለሳ እና ደምቢያ አካባቢዎችም “ጣና” እና “ጉዛራ” የሚባሉ የሽንብራ ዝርያዎችን፣ “መልካም” የሚባል ማሽላን በማሰራጨት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርጓል ነው ያሉት። በተጨማሪም የሩዝ እና የቅመማ ቅመም ዝርያዎችን በመልቀቅ እና በማባዛት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋጽዖ እያበረከተ መኾኑን አስረድተዋል።
በቆላማ አካባቢዎችም ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የተለያዩ የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተር፣ የጥጥ፣ የሱፍ ዝርያዎች ወደ ልማት መለቀቃቸውንም ነው ዶክተር ቴዎድሮስ የገለጹት። ለአብነትም “ጠረፍ ወርቅ” የሚባል አኩሪ አተር፣ “ማር ዘነብ” የሚባል ሰሊጥ፣ “ጃን ተከል” የሚባል ጥጥ እና ሌሎችንም በርካታ ዝርያዎችን በሥፋት ወደ ልማት ማስገባቱን አብራርተዋል።
የምርምር ማዕከሉን ለማጠናከር የማባዣ ቦታ እጥረት እያጋጠመ መኾኑንም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። ለዚህም ማዕከሉ በሚሠራባቸው አካባቢዎች የሚመለከታቸው የመንግሥት አሥተዳደሮች አስፈላጊውን የሥራ ቦታ ድጋፍ በማድረግ ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።
#ሑመራ_ጎንደር#ዳባት#ደባርቅ#ሰሊጥ#
አሚኮ-ጥቅምት_29_2019_ዓ.ም
✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበሐረሪ ክልል 5 ሺህ ሔክታር መሬት የሚሸፍን የበጋ መስኖ ልማት ተጀመረ።
Next article🌊ከቀይ ባሕር ማዶ ያለው እውነት – የኢትዮጵያ የህልውና፣ የደህንነት እና የኢኮኖሚ ትግል