🌊ከቀይ ባሕር ማዶ ያለው እውነት – የኢትዮጵያ የህልውና፣ የደህንነት እና የኢኮኖሚ ትግል

6

ታሪካዊ ስህተቶች፣ የውጭ እና የውስጥ ሴራዎች ኢትዮጵያን ለበርካታ ዓመታት ከቀይ ባሕር እንድትገለል አድርገዋታል። የሥራ አመራር አማካሪ እና ፖለቲከኛ ጌትዬ ትርፌ (ዶ.ር) ጉዳዩ ለሀገሪቱ የህልውና፣ የሉዓላዊነት እና የኢኮኖሚ አንገብጋቢ ስብራት መኾኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ወደብ አልባነት የሀገሪቱን ሚስጥራዊ እንቅስቃሴዎች ለሦስተኛ ወገን በማጋለጥ ለሉዓላዊነት አደጋና ለውጭ ግፊት እየዳረጋት መኾኑን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባደረገችው ጦርነት የበላይነት ባሳየችበት ወቅት የተጣለባት ወታደራዊ ማዕቀብ ማሳያ በመኾኑ ወደ ባሕር የመመለስ አሁናዊ መሻቷ ፍጹም ተገቢ አደርጎታል።

“የኢትዮጵያ የባሕር በር አልባነት ከጎረቤቶቿ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ” በሚለው ጥናት እንደተመላከተው ኢትዮጵያ በዓመት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለወደብ ኪራይ ወጪ ታደርጋለች። በፕሮፌሰር ተባረክ ልኬ እና ባልደረባቸው የተካሄደው ይኸው ጥናት የኪራይ ወጪው ለልማት ሊውል የሚችል ከፍተኛ ሀብት እንዲባክን አድርጓል።

ጥናቱ የወደብ ጥገኝነቱ የሀገሪቱን የፖለቲካ ነፃነት እና የድርድር አቅም በማዳከም በሌሎች ተጽዕኖ ሥር እንድትወድቅ ምክንያት ሲኾን መቆየቱን አመላክተዋል።

መማር አያሌው በበኩላቸው “የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍለጋ፡- መብቶች፣ ነባራዊ ሁኔታዎች እና ቀጣናዊ ዕድሎች” በሚለው ጥናታቸው እንዳመላከቱት የኢትዮጵያ የወደብ ኪራይ እና የትራንስፖርት ወጪ ከውጭ ከምታስገባው ዕቃ ጠቅላላ ዋጋ እስከ 40 በመቶ ይሸፍናል። ይህም ከዓለም አቀፍ አማካይ አምስት እጥፍ ከፍ ያለ በመኾኑ የዜጎችን ኑሮ ውድነት አባብሶ የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነቷን በእጅጉ እንደ ጎዳት በማስረጃ አመላክተዋል።

የወደብ አለመኖር በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዋስትና ላይ ከፍተኛ አደጋ እንደፈጠረ ይኸው ጥናት አረጋግጧል። የዓለም የኢነርጂ ኤጀንሲ እንደሚገልጸው ቀጥተኛ የወደብ ተደራሽነት ማግኘት የአቅርቦት መስተጓጎል ስጋትን በማስወገድ እና የኢነርጂ ወጪዎችን ከ15 እስከ 20 በመቶ በመቀነስ ሀገራዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

መማር አያሌው፣ በጥናታቸው የወደብ አለመኖር ኢትዮጵያን ዓለምአቀፍ ዋጋው 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር ኾኖ እ.አ.አ በ2030 ለአፍሪካ 400 ቢሊዮን ዶላር ያስገኛል ተብሎ ከሚገመተው ሰማያዊ (ከውኃማ አካላት) ኢኮኖሚ ውጭ እያደረጋት ይገኛል። ጎረቤት ሀገራት የባሕር ሀብቶቻቸውን ሲያለሙ ኢትዮጵያ ግን ከቀይ ባሕር ገበታ ተገፍታ በመሬት ላይ በሚገኙ ሀብቶች ብቻ እንድትወሰን አድርጓታል።

የባሕር ጠረፍ ቁጥጥር ማጣት ከጎረቤት መረጋጋት ጋር የተሳሰረ የደህንነት ተጋላጭነትና የውጭ ግፊት እንዲባባስ ያደርጋል። የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለትግራይ ኀይሎች በምጽዋ ወደብ በኩል ተላልፎ የነበረ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ በመከላከያ ሠራዊቱ ቁጥጥር ሥር መዋሉን መናገራቸው ለዚህ ማሳያ ነው።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ለ130 ሚሊዮን ሕዝብ ህልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል። በጣና ከፍተኛ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገሪቱ ይህንን ፍላጎት በሰላማዊ መንገድ እና በጋራ ጥቅም ላይ ተመስርታ ለማሳካት ጥረቷን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

‎#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#AMECO#SeaGate#Sovereignty#Ethiopia
አሚኮ-ጥቅምት_29_2019_ዓ.ም

✍️:- በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ተስፋ ሰጪ ሥራዎች- ከድንች እስከ ነጭ ወርቅ ምርታማነት
Next articleየሐረሪ ክልል ከ2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ለ16 አልሚዎች በክልሉ እንዲያለሙ የመሥሪያ ቦታ በምደባ ተደረገ።