🇪🇹 የክንደ ብርቱዎች ጽኑ እናት

7

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያን የዘመናት የታሪክ ጥልቀት፣ ፈተናዎችን የማለፍ አቅም እና የሕዝቧን የማይበገር ሥነ-ልቦና ሲገልጹ “ኢትዮጵያ በሠፈር ጎረምሳ የምትሰበር ሀገር አይደለችም፤ 100 ሚሊዮን የቁርጥ ቀን ልጆች ያሏት የክንደ ብርቱዎች እናት ናት” ማለታቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠሟትን የውስጥ እና የውጭ የዘመናት ጥቃቶች በድሎት ሳይኾን በልጆቿ አጥንት እና ደም ተቋቁማ የቆመች ሀገር ናት፤ ጊዜያዊ ጀብደኞችም ይህንን የጽናት መሠረት መናድ አልቻሉም።

የዓድዋን ድል ጨምሮ በበርካታ የታሪክ አውድማዎች ላይ የታየው ሐቅ ኢትዮጵያ በልጆቿ የጋራ ክንድ ታሪኳን ሳታስደፍር እና የውጭ ወራሪዎችን በደረት መመከቻነት እየመለሰች መሻገሯን ነው።

ኢትዮጵያ ዛሬም ጠላቶቿ ከሚያስቧት እና ከሚያቅዱት በላይ የሚቃጡባትን ጥቃቶች በብቃት እያከሸፈች ትገኛለች። የሀገሪቱን ሕልውና ለመጠበቅ ሲባል የመከላከያ ሠራዊቷን አቅም ዓለም በደረሰበት ዘመናዊ የትጥቅ ቴክኖሎጂ፣ በዲጂታል ወታደራዊ ሳይንስ እና በሠለጠነ የሰው ኃይል እያጠናከረች ነው።

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የሉዓላዊነቷን ደኅንነት በራሷ አቅም ማረጋገጥ የሚችል፣ በማናቸውም የጂኦፖለቲካ ንፋስ የማይናወጥ ጽኑ የጸጥታ ምሽግ አላት። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ሰላም ከማጽናት ባለፈ የጠላቶችን ስልታዊ ስሌት በመቅደም በላቀ ዝግጅት ላይ ይገኛል።

ጽኑ መሠረቱ እና እያደገ የመጣውን ሀገራዊ ቁመና ለማፍረስ ግን ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ዛሬም ከውስጥ አጥፊዎች እና ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች (ከኤርትራ እና ከግብጽ) ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን አንድነት፣ መረጋጋት እና የብልጽግና ጉዞ ለማዳከም ደከመኝን አላወቀም።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በውስጥ እና በውጭ ጠላቶች ሴራ አልተበገረችም። በሕዝቧ አቅም እና በታሪካዊ ጽናት የጥፋት ኃይሎችን ዓላማ እያከሸፈች በልማት እና በሜጋ ፕሮጄክቶች የብልጽግና ጉዞዋን በድል ቀጥላለች።

ኢትዮጵያ ከማንኛውም ፈተና በንጹሕ ወርቅነት ወጥታ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ከዳር ለማድረስም የልጆቿን አንድነት እና ክንድ መተማመኛ አድርጋለች።

#አሚኮ #SovereigntyFirst ​#ENDF

#GuardiansOfEthiopia

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_27_2019_ዓ_ም

✍️ በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🗺️ቀይ ባሕር እና ዓባይ-የኢትዮጵያ ገናናነት እና የታላቅነት ማሳያ
Next articleከሰብል ሥብሠባ እስከ ጎተራ፤ ለምርት ጥራት ዘመናዊ አሠራርን መተግበር !