🗺️ቀይ ባሕር እና ዓባይ-የኢትዮጵያ ገናናነት እና የታላቅነት ማሳያ

7

 

የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በቀይ ባሕር እና በዓባይ ሸለቆ መካከል የተመሠረተ መኾኑን ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ. ድሌቦ “የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብ እና የመንግሥት ታሪክ” በሚል መጽሐፋቸው ላይ አስቀምጠዋል።

በታላቁ የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ የኢትዮጵያ ምድር በሰሜን ምዕራብ እና በደቡብ ምሥራቅ የተራራ ሠንሠለቶች ሲከፈል በውስጡ ወደ ውጭ ሀገራት የሚያቋርጡ በርካታ ትላልቅ ወንዞች መኖራቸውንም ያትታሉ።

የኢትዮጵያ ወንዞች ሀገሪቱን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኢኮኖሚ፣ በባሕል እና በፖለቲካ የሚያገናኙ የሕይወት ምንጭ፤ የጂኦ ፖለቲካ ገጽታ ናቸውም ይላሉ።

ታሪክ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ፣ ከእስያ፣ ከአውሮፓ አሕጉራት እና ሕዝቦች ጋር ቀይ ባሕርን በመጠቀም የንግድ እና የውጭ ግንኙነትን ትፈጽም ነበር።

በተለያየ ጊዜ የሚነሱ የሀገራት ነገሥታት እንደ ዘመኑ የዓለም ኹኔታ እና አሠራር በዘመኑ ከነገሡ የኢትዮጵያ ነገሥታት ጋር በቀይ ባሕር እና በዓባይ ሸለቆ በሮች ግንኙነት ያደርጉ ነበር።

በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ ነገሥታት የቀይ ባሕርን ፈጣን የንግድ እንቅስቃሴ ለማስቆም የሚጥሩ የባሕር ወንበዴዎችን ከሌሎች መንግሥታት ጋር በመኾን እርምጃዎችን በመውሰድ የቀይ ባሕር ሰላም እና ደኅንነትን ያስጠብቁ እንደነበር ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ. ድሌቦ በመጽሐፋቸው ገልጸዋል።

ዘመናት አልፈው በታሪክ እጥፋት እና በፖለቲካ ሤራ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ተገለለች። ይሁን እንጂ በሰላማዊ ዲፕሎማሲ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ዳግም ወደ ቀይ ባሕር ለመመለስ በትኩረት እየሠራች ነው።

ከባሕር በር ብትርቅም ከኢትዮጵያ አልፎ የቀጣናውን ደኅንነት መጠበቅ የሚችል ጠንካራ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ገንብታለች። ወደ ባሕር ስትቀርብ ደግሞ የበለጠ ኃይሏ ይደረጃል። ዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂዎችን፣ ድሮኖችን፣ የጦር አውሮፕላኖችን በመታጠቅ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት አለኝታ ለመኾን ተዘጋጅታለች።

የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መመለስ የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣና ሰላም የሚያጸና፣ የአማጺያን ቡድኖችን የጥፋት መንገድ የሚያስቆም፣ የአፍሪካን ተደማጭነት የሚያጎላ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያሳልጥ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መኾኑን በርካታ የፖለቲካ ምሁራን ተንታኞች ሲገልጹ ይስተዋላል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዝግጅት በአፍሪካ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል። ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አለኝታ እና መከታ ለመኾን ኢትዮጵያ እየሠራች መኾኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትን ለማስቀረት ዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂ የታጠቀ ሰላም እና መረጋጋትን የሚፈጥር ጠንካራ ሠራዊት መገንባቷንም ገልጸዋል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_27_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበወራቤ ሆስፒታል በሰዓት 60 ኪዩቢክ ሜትር ኦክስጅን የሚያመርት ፋብሪካ ተመረቀ።
Next article🇪🇹 የክንደ ብርቱዎች ጽኑ እናት