በወራቤ ሆስፒታል በሰዓት 60 ኪዩቢክ ሜትር ኦክስጅን የሚያመርት ፋብሪካ ተመረቀ።

4

 

አዲስአበባ፡- 27/02/2019 (አሚኮ) – በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሰዓት 60 ኪዩቢክ ሜትር ኦክስጅን የማምረት አቅም ያለውን ፋብሪካ አስመርቋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ፋብሪካውን በመረቁበት ወቅት፣ ከዚህ ቀደም የነበረውን የኦክስጅን እጥረትና አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የማምረቻ ማዕከላትን ማስፋፋት እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በፊት 10 የኦክስጅን ማምረቻዎች ብቻ እንደነበሩና አሁን ቁጥራቸው ከ65 በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

የሆስፒታሉ ሲኒየር ባዮሜዲካል ኢንጂነር ጀማል ጥላሁን በበኩላቸው፣ ማዕከሉ የኦክስጅን አቅርቦትን ከማረጋጋት ባለፈ በአካባቢው ለሚገኙ ሌሎች የጤና ተቋማትም ኦክስጅን ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በጤና ሚኒስቴር የሚመራው ልዑክ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚገኙ የጤና ተቋማት ጉብኝት አድርጓል።

በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ጤና ጣቢያና የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ከተጎበኙት ተቋማት መካከል ይገኙበታል።

በጉብኝቱም የዲጂታል ጤና አገልግሎት፣ የሪፈራል ሥርዓት፣ የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት እንዲሁም የሕክምና ሥልጠና አቅምን ለማጠናከር የሚደረጉ ሥራዎችን ተመልክተዋል።

በአየለ መስፍን

Previous articleየአዋሽ- ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ የባቡር መስመር የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ግንባታ እየተካሄደ ነው።
Next article🗺️ቀይ ባሕር እና ዓባይ-የኢትዮጵያ ገናናነት እና የታላቅነት ማሳያ