
በሐረሪ ክልል በሆቴል፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ የኢንቨስትመንት ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት የሦስት ወራት የሥራ
አፈፃፀም ገምግሟል። በቀረበው ሪፖርትም በክልሉ በኢንቨስትመንት ፍቃድ መሬት ወስደው ወደ ሥራ ባልገቡ አልሚዎች ላይ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ኢንቨስትመንት ፍቃድ ስረዛ ርምጃ መወሰዱ ተመላክቷል። በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ቅንጅታዊ
አሠራርን በማጠናከር የክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲጎለብት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ክልላዊ ፋይዳ ባላቸው ዘርፎች ላይ የሚሰማሩ አካላት በተለይም በሆቴል፣ በማኑፋክቸሪንግና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።
በተለይም በራሳቸው ይዞታ ላይ ለሚያለሙ ባለሃብቶች ቅድሚያ እንደሚሰጥም ርዕሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ተቋማትን ቅንጅታዊ አሠራር በማጠናከር የክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲጎለብት ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ
አልሚዎች የሥራ እንቅስቃሴን ልዩ ትኩረት በመስጠት በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት ይገባል ነው ያሉት። በክልሉ የተጀመረው የኢንቨስትመንት ክትትልና ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
