
ሰላም የሀገር ልማት እና ዕድገት የማዕዘን ድንጋይ ነው። የአማራ ክልል ሕዝብ በየጊዜው የሀገር ዘብ የኾነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመደገፍ እና ግጭት የሚጠነስሱ ኀይሎችን በማውገዝ ወደ አደባባይ ወጥቶ ትልቅ እና ታሪካዊ መልዕክት እያስተላለፈ ይገኛል። ሕዝቡ በድምጹ
ያስተጋባው እውነት ለክልሉ መፃኢ ዕድል እና አስተማማኝ ሰላም ከፍተኛ ፋይዳ አለው። በእርግጥም ሕዝቡ ከግጭት እና ከእርስ በርስ ከመተላለቅ ይልቅ ዘላቂ ሰላምን፣ የሕግ የበላይነት መከበርን እና ልማትን በእጅጉ እንደሚሻ በአደባባይ አረጋግጧል። የደኅንነት እና የሰላም ዋስትና
የኾነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት እየከፈለው ላለው መስዕዋትነት በአደባባይ ያደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍም ለሠራዊቱ ትልቅ አቅም በመፍጠር ሚናው የላቀ ነው። ሰልፉ በሕዝብ ስም እየማሉ እና እየነገዱ በየጊዜው ግጭት የሚጠምቁ፣ ጦርነት የሚቀሰቅሱ እና ጥላቻን የሚሰብኩ ኀይሎችን
የጥፋት አጀንዳ በማጋለጥ እና በማውገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በተለይም በዘር፣ በብሔር እና በእርስ በርስ ግጭት የተከፋፈሉ ልቦችን አፍርሶ የጋራ መግባባትን እና ሰላማዊ አብሮነትን ገንብቷል። ታዲያ ሕዝቡ ይህን ሰላም ወዳድነቱን በዕለት ተዕለት ተግባሩ ማሳየት፣ ከግጭት
ቀስቃሾች ራሱን ማራቅ እና ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት ይገባዋል። የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ጽንፈኝነት የሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል፤ ባሕልን እና እሴትን ያጠፋል፤ አብሮነትን ይሸረሽራል፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን
ያመጣል ይላሉ። ጽንፈኝነትን መታገል የታቀዱትን ዕቅዶች ለማሳካት፣ የክልሉን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት እና የክልሉን ሁለንተናዊ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ መኾኑንም አንስተዋል። መንግሥትም ቢኾን የሕዝቡን ደኅንነት እና ሰላም ያለ ቅድመ ሁኔታ ማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን
በማስፈን የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በመጠበቅ ኀላፊነቱን መወጣት አለበት ይላሉ። “በየደረጃው ያለው የክልሉ መሪ ከሕዝቡ ጋር በትብብር እና በቅንጅት ሲሠራ የክልሉ ሰላም በዘላቂነት ይፈታል፤ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ የፖለቲካ መሪው ጽንፈኝነትን ከልብ መታገል አለበት”
ብለዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ በየጊዜው እያሰማ ያለው የሰላም ድምጽ በክልሉ ብቻ ሳይኾን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ የሰላም ጥረቶች ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
