
በአማራ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተከናወኑ የመንግሥት እና የፓርቲ ተግባራት አፈጻጸም በባሕር ዳር ከተማ እየተገመገመ ነው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ባለፈው ዓመት የተመዘገቡት ስኬቶች ለ2019 በጀት ዓመት ተግባራት ትልቅ መነሳሳትን የፈጠሩ ናቸው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የክልሉን ጸጋ መሠረት ያደረጉ ዕቅዶች ተዘጋጅተው እና መግባባት ተፈጥሮባቸው ወደ ተግባር መገባቱን አንስተዋል።
ከተለመደው አካሄድ በመውጣትም በዕውቀት ላይ የተመሠረተ፣ የክልሉን አቅም ያማከለ እና አሳታፊ በኾነ መንገድ በመሥራት ክልሉን ለመለወጥ ቁርጠኝነት ተወስዶ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። በዚህም በሁሉም ዘርፎች ስኬቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
በተናበበ እና በጠንካራ አመራር በተሠራው ሥራም የውጭ ኀይሎች ከሕገወጡ ሕወሃት እና ከሌሎች የውስጥ ኀይሎች ጋር ተባብረው ያቀዱትን የጥፋት ተልዕኮ ማምከን መቻሉንም አመላክተዋል።
በየደረጃው ያለው የክልሉ መሪ ከሕዝቡ ጋር አንድ በመኾን ተቀናጅተን ስንሠራ የክልሉን ሰላም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እየፈታን እንሄዳለን ነው ያሉት። ይህንን እውን ለማድረግም “መላው መሪ ጽንፈኝነትን ከልብ መታገል ይገባዋል” ብለዋል።
ጽንፈኝነት የሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል፤ ባሕልን እና እሴትን ያጠፋል፤ አብሮነትን ይሸረሽራል፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ያመጣል ነው ያሉት። ጽንፈኝነትን መታገል የታቀዱትን ዕቅዶች ለማሳካት፣ የክልሉን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት እና ለሀገር አቅም የኾነ ተወዳዳሪ ክልል ለመገንባት ወሳኝ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማ አሥተዳደሩ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በተለይም ከተማዋን ውብ፣ ምቹ እና ለጎብኝዎች ተመራጭ ለማድረግ የተጀመሩት የጣና ዳር ልማት እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መኾናቸውን አንስተዋል። በርካታ ኢንዱስትሪዎች እና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እየተስፋፉባት እንደሚገኙም ነው ያመላከቱት።
ከተማዋን 24 ሰዓት ኢኮኖሚ የምታመነጭ ለማድረግ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_26_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
