
የደቡብ ጎንደር ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ታራሚዎችን በሥነ-ምግባር እና በሙያ በማነጽ አምራች ዜጋ እንዲኾኑ እያደረገ ነው።
ተቋሙ ሕግ እና ሥርዓትን የማስከበር ተልዕኮውን እየተወጣ፣ ጎን ለጎን የውስጥ ገቢውን ለማሳደግ እና የታራሚዎችን የምግብ ፍጆታ ለማሟላት በስፋት እየሠራ መኾኑን የመምሪያው ኀላፊ ኮማንደር የቆየ ዋለ ገልጸዋል።
በግብርናው ዘርፍ በቆሎ እና ባቄላ በስፋት በማምረት ባለፈው በጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የውስጥ ገቢ ማግኘት ተችሏል ብለዋል። በእንስሳት እርባታ ዘርፍም የወተት ላሞች ምርታማነት እንዲጨምር ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በተደረገ ሙያዊ ክትትል የተሻለ የእንስሳት ተዋጽኦ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
አርዓያነት ያለው ይህ የልማት እና የማነጽ እንቅስቃሴ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሊሰፋ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ ታራሚዎች መምሪያው ያመቻቸላቸው የትምህርት እና የክህሎት ማደራጃ ዕድል በሕይወታቸው ላይ በጎ መሻሻል ማምጣቱን ገልጸዋል። ባገኙት ዕውቀት እና ሙያ ተስፋቸው መታደሱን የጠቆሙት ታራሚዎቹ ከማረሚያ ቤት ሲወጡ በተሰማሩበት የሙያ መስክ ለሀገራቸው አምራች ዜጋ ለመኾን ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ታራሚዎችን በሥነ-ምግባር እና በሙያ በመቅረጽ በኩል እያከናወነ ያለው የልማት እና የማነጽ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፡ ተክለብርሃን ፈንታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
