
ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰው ኃይል ብቃት፣ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም፣ በሳይንሳዊ ሥልጠና እና በጠንካራ ተቋማዊ ዲሲፕሊን ተገንብቶ የዘመኑን ቁመና በግልጽ አሳይቷል።
በተለይም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘመናዊ ጄቶችን፣ የላቁ ድሮኖችን እና ጠንካራ የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን በመታጠቅ በሰማይ፣ በባሕር ዳርቻዎች እና በየብስ ሀገሩን በብቃት የሚጠብቅ ብሔራዊ ኩራት ኾኗል። ይህ ወታደራዊ ዝግጅት ኢትዮጵያን ለመተንኮስ በሚያልሙ የውስጥ እና የውጭ ጠላት ኃይሎች ለመጠበቅ የሚያስችል ጽኑ መሠረት ነው።
ሠራዊቱ ዘመናዊ የጦር ትጥቅ እና የቴክኖሎጂ አቅም በመገንባት የውስጥ ባንዳዎችን ጨምሮ የውጭ ጠላቶችን በመከላከል እና የቀጣናውን ሰላም በማስፈን ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በአሕጉር አቀፍ ደረጃ በሰላም አስከባሪነት እና በደኅንነት ትብብር የተገኘው እውቅና እና ክብር የዚሁ ተቋማዊ ብቃት እና የሠለጠነ ሠራዊት ማሳያ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያዩ ጊዜያት እንደገለጹት፤ “የመከላከያ ሠራዊታችን የአሸናፊነት ምሥጢሩ የአባቶቹን አርበኝነት መውረሱ እና ለሀገር ሕልውና ሲል በማይበገር የጸና መንፈስ መቆሙ ነው ማለታቸው ይታወሳል። ክህደት ቢደርስበትም ከግራ እና ከቀኝ መከራ ቢያንዣብብበትም ሠራዊቱ በወታደራዊ ብቃት እና በጽናት ተነስቶ የሀገርን ሉዓላዊነት አስከብሯል”።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ዛሬ ያለው መከላከያ ከማንኛውም አቅጣጫ የሚመጣን አደጋ ለመመከት ዝግጁ የኾነ፣ በዲሲፕሊን እና በዘመናዊ አሠራር የታነጸ የማይበገር የሰላም ጠባቂ ነው ብለዋል።”
የመከላከያ ሠራዊቱ የማይበገር ኃይል ኾኖ የቆመው ከቴክኖሎጂው ባሻገር ከሕዝቡ ጋር ባለው ጥልቅ ትስስር ጭምር ነው።
ሠራዊቱ ከሕዝቡ የተወለደ፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነትን የተላበሰ እና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም እና የሕዝቡን ሰላም ከሁሉ በላይ የሚያስቀድም ነው። ወታደራዊ መዋቅሩ የብሔር፣ የቀለም እና የባሕል ልዩነቶች ሳይገድቡት የሀገር ማሠሪያ የኾነ የማይበጠስ ገመድ ኾኗል።
ይህ በመስዋዕትነት ሀገርን የማስቀጥል ብርቱ ጉዞ እና የአርበኝነት ተጋድሎ ሠራዊቱ ለሀገሩ የገባውን ቃል ኪዳን ከግል ሕይወቱ በላይ እንደሚያስቀድም ሕያው ማሳያ ነው። የዛሬው መከላከያ ሠራዊት የነገዋን የበለጸገች፣ የጸናች እና የተከበረች ኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ የሚከፍለው መስዋዕትነት ታሪክ በየጊዜው የሚዘክረው ነው።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
