“እርስት በሺህ ዓመቱ ለባለቤቱ”

8
በታሪክ ረጅም ዘመን በምጣኔ ሃብት፣ በወታደራዊ እና በባሕል ደረጃ የኤደን ባሕረ ሰላጤን፤ የቀይ ባሕር አካባቢን፤ የአፍሪካ ቀንድን እና የአረቢያ ልሳነ-ምድርን ሁሉ ይቆጣጠሩ የነበሩ ገናና መንግሥታት እና ሀገራት በየታሪክ አጥቢያው ብቅ ጥልቅ እያሉ ታይተዋል፡፡
ከእነዚህ ጥንታዊ ሥልጡን እና የጎላ ተጽዕኖ ከነበራቸው አብሪ ኮኮብ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሀገር ናት፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ እስከ 7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ከሮም፣ ከፋርስ እና ከቻይና ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ጋር የሚስተካከል የአክሱም ሥልጣኔን ለዓለም ያስተዋወቀችው ኢትዮጵያ ታላቅ የባሕር ላይ ንግድን፣ ወታደራዊ ኃይልን እና የራሱን ገንዘብ ቀርጾ የሚጠቀም ፍጹም ገናና መንግሥት መሥርታ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። አዱሊስ የተሰኘው ታዋቂ ወደቧም የቀይ ባሕር ንግድ እምብርት ተደርጎ ይወሰዳል።
የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ከባቢ ከጥንት ጀምሮ ሜዲትራኒያንን፣ አፍሪካን፣ አረቢያን እና ሕንድን የሚያገናኝ የንግድና የጂኦ-ፖለቲካ ማዕከል በመኾኑ ገናና መንግሥታት ክንፎቻቸውን የዘረጉበት እና ታሪካዊ አሻራቸውን ያሳረፉበት የዓለም ፖለቲካ የስበት ማዕከል የኾነ ወሳኝ ቀጣና ነበር።
ቀጣናው የንግድ መሸጋገሪያ ኮሪደር ብቻ ሳይኾን የተለያዩ ሕዝቦች የባሕል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ እና የቴክኖሎጂ ልውውጥ የተካሄደበት ታሪካዊ የኃይል መቆናጠጫ እርካብ እና የሥልጣኔ መድረክም ጭምር ነበር። ቀጣናውም ቢኾን የአካባቢውን ሀገራት ብቻ ሳይኾን በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው ከቀጣናው በእጅጉ የራቁ ኃያላን መንግሥታትን እና ልዕለ ሀገራትን ትኩረት የሚስብ ተፈላጊ አካባቢም ጭምር ነው፡፡
ፖል ሉንዴ እና አሌክሳንደራ ፖርተር “ትሬድ ኤንድ ትራቭል ኢን ዘ ሬድ ሲ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት የጥናት መጽሔት ላይ እንዳሰፈሩት የአካባቢው ተፈጥሯዊ ሁኔታ በተለይም የወቅቶች የነፋስ አቅጣጫ መለዋወጥ እና የባሕር ዳርቻዎቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በተለያዩ ዘመናት በነበሩ ታላላቅ መንግሥታት እና ኢምፓየሮች የባሕር ኃይል ስትራቴጂ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል ይሉናል።
በተመሳሳይ ሰርገው ኃብለ ሥላሴ “የጥንታዊው እና መካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል ርዕስ 1972 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፋቸው እንደነገሩን የዚህ ቀጣና ታሪክ የተቃኘው በሀገር በቀል ኃይሎች እና በተሻጋሪ የባሕር ኃይሎች መካከል በሚደረግ የማያቋርጥ እና የበላይነትን ለመጫን በሚደረግ ትግል ነው።
ከሩቅም ከቅርብም በሚሰባሰቡ ኃይሎች እልህ አስጨራሽ ትርምስ እና ዘርፈ ብዙ መስተጋብር በማያጣው በዚህ አካባቢ ከጥንት እስከ ዛሬ ስትራቴጂክ ተፈላጊ ኾኖ ለመውጣት ውስብስብ ሴራዎች፣ እልፍ ፍትጊያዎች እና ውድ ዋጋዎች ተከፍለዋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ ከባቢ የሚዘወተረው ጥንታዊ የውክልና ጦርነት እና የኃይል ሚዛን መቀያየርም ከባቢውን የአጭር እና ረጂም ዘመናት ተጽዕኖዎች ሰለባ አድርጎታል የሚሉት የዘርፉ ምሁራን በርካታ ናቸው፡፡ ከረጂም ዘመን ተጽዕኖዎቹ መካከል አንዱ ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ጂኦ-ፖለቲካዊ ተጋላጭነት መፍጠሩ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
በቀይ ባሕር አካባቢ የተደረገው የበላይነት ትግል በአካባቢው ያሉ ሀገራትን ህልውና ብቻ ሳይኾን የዓለም አቀፉን የንግድ እና የኃይል ሚዛን የመዘወር አቅምም ነበረው፡፡ ይህ ታሪካዊ ሀቅ ደግሞ በዛሬው ዘመናዊ የጂኦ-ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥም ቢኾን ተዛማጅነቱ የጎላ ኾኖ ይስተዋላል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ቀጣና ተጋሪ ሀገራት ተርታ ለመፋቅ የተደረጉት ሙከራዎች በአንድ ጀምበር የመጡ እና በቅርብ የተወለዱ ሃሳቦች እንዳልነበሩ እናያለን፡፡ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ቀጣና የማራቁ ሴራ ከ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይጀምራል፤ ያም ኾኖ ግን እስከ መካከለኛው ዘመን ድረስ ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰፊ ግዛት እና ከፍ ያለ ተጽዕኖ ነበራት፡፡
የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ መንግሥታት በዋናነት የዛጉዌ እና ሰሎሞናዊው ሥርወ-መንግሥታት በኤደን ባሕረ ሰላጤ በኩል የሚገኘውን የዘይላ ወደብ በመጠቀም የውጭ ንግድ ግንኙነታቸውን ቀጥለው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡
ሪቻርድ ፓንክረስት “ዘ ኢትዮጵያን ቦርደርላንድስ” በተሰኘው የጥናት ድርሳናቸው በቀጣናው የተስተዋሉ የመካከለኛው ዘመን ግጭቶች ዋነኛ ምክንያት የዘይላን እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ የንግድ መስመሮችን የመቆጣጠር ምጣኔ ሃብታዊ ፍላጎት ነበር ይሉናል። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ የተከሰተው የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ቅርምት በቀጣናው ሀገራት የተለየ ፖለቲካል ምህዳር እንዲፈጠር ምክንያት ኾነ፡፡
በ1869 የሱዌዝ ካናል መከፈትን ተከትሎ የቀይ ባሕር ኮሪዶር ለአውሮፓውያን ኃይላት እጅግ ተፈላጊ እየኾነ መጣ።
ጣሊያን በአሰብ እና በምፅዋ በኩል በመግባት አካባቢውን በቅኝ ግዛትነት በመቆጣጠር “ኤርትራ” የምትባል ሀገር በመፍጠር ሀገር በቀል ሞግዚት አስቀመጠች፡፡ ከዚህ በኋላ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የተፈጠረው ሁሉ ምንጩ የአስተሳሰብ ሞግዚቶች እየተቀባበሉ ያራመዱት ስሁት ትርክት እንደነበር እንረዳለን፡፡
የዛሬን አያድርገውና ሌላው ሁሉ ቀርቶ ከጥቂት ዓመታት በፊት ስለባሕር በር ጥያቄ ማንሳት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድባብ ውስጥ ዋጋ የሚያስከፍል መርገምት እንደነበር ስናስብ የተሠራንበትን ሳይኾን የሠሩብንን እንድንኖር መገደዳችን እንረዳለን፡፡
የእኛ ሰው በብሂሉ “እርስት በሺህ ዓመቱ ለባለቤቱ” ይላል፤ የዚህ ዘመን ትውልድ ወደ ቀደመ ታሪኩ እና ክብሩ የሚመለስበት ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ የቀረበ ይመስላል፡፡
ሌላው ቢቀር የቀይ ባሕር ተጋሪ ሀገራት ነበርን፤ መኾንም ይኖርብናል የሚለው እሳቤ በትውልዱ ዘንድ መቀንቀኑ ግማሽ መንገድ ያክል ያስጉዛል፡፡ ኢትዮጵያ ዳግም ወደ እርስቷ ተመልሳ ያንን ገናና ታሪክ የምትመልስበት ዘመን ሩቅ አይኾንም፡፡
✍️ በታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleለኅብረተሰቡ ትልቅ እፎይታ የሰጠው የአማራ ክልል የከተማ አውቶብሶች ስምሪት እና የኮሪደር ልማት!
Next article“የሰላማችን እና የሉዓላዊነታችን ምሰሶ”