“ኢትዮጵያዊያን አይረሷትም፤ ስለፍቅር ሲሉም ቂም አይዙባትም”

13
አንዳንድ ቀናት አሉ ትውልድ ሁሉ በእንባ የሚያስታውሳቸው፣ ለዘለዓለም እንዳይደገሙ የሚመኛቸው፣ መማሪያ ይኾኑ ዘንድ የሚሻቸው፣ መከራ የሚታሰብባቸው፣ ክህደት የሚታወስባቸው፣ ልብ በሀዘን የሚያንሰላስላቸው፣ ታሪክ በጥቁር መዝገብ ላይ የሚያሠፍራቸው፣ ሀገር ወዮ ብላ የምታዝንባቸው፣ በልቧ መዝገብ ውስጥ የማታጠፋቸው፡፡
አንዳንድ ቀናት አሉ ሀገር ዘመናት አልፈው ዘመናት በተተኩ ቁጥር እንዳይደገሙ የምትመክራቸው፣ ለትውልድ ማስተማሪያ የምታደርጋቸው፡፡
ይህች ቀን በለቅሶ ትታሰባለች፣ በሀዘን ትታወሳለች፣ በእንባ ትዘከራለች፡፡ የከፋች ቀን ናትና እንዳትደገም ማስጠንቀቂያ ትኾናለች፡፡ ኢትዮጵያዊያን
አይረሷትም፣ ከታሪካቸው መዝገብ ላይ አያጠፏትም፣ ከልባቸው ጽላት ላይ አይፍቋትም፡፡ ግን ስለ ፍቅር ሲሉ ቂም አይዙባትም፣ ስለ ሀገር ሲሉ ለበቀል አይነሱባትም፣ ስለ ይቅርታ ሲሉ ጦር አይማዘዙባትም፣ ስለ ሰላም ሲሉ ክፉነቷን ያስባሉ እንጂ ሌላ ክፋት አይሠሩባትም፣ ስለ አንድነት
ሲሉ እንዳትደገም ያስተምሩባታል እንጂ አይደግሟትም፡፡ ክፉ ቀን ክፋቷ ይበቃልና፡፡ ክፉን በክፉ ከመለሱት ምድር በደም ትጨቀያለች፣ ክፉን በክፉ ከመለሱት ምድር በዋይታ ትመላለች፣ የሰው ነብስ ትረክሳለች፣ የጸናች ሀገር የመከራ ማቅ ታጠልቃለች፡፡ ክፉውን በፍቅር ሲመልሱት
የተጣሉት ይታረቃሉ፣ የተለያዩት ይገናኛሉ፣ የካዱት ይጸጸታሉ፣ የወጉት ያፍራሉ፣ ሥራቸውን ይረግማሉ፣ ዳግም እንዳይደገም በልባቸው ቃል ይገባሉ፡፡ ክፉን በፍቅር ሲመልሱት ምድር ሰላም ትኾናለች፣ የጸናች ሀገር ትጸናለች፡፡ በዚህች ቀን ሀገር የሚጠብቀውን ወጉት፣ ሀገር
የሚያስከብረውን ካዱት፣ እስከ መቃብር ድረስ የሚታመነውን እምነት አጎደሉበት፣ የኮዳ ውኃ እየጠጣ ወይን የሚያስጠጣውን ገደሉት፣ በምሽግ እያደረ በቅንጡ እልፍኝ የሚያሳድረውን አሰቃዩት፣ መለዮውን ሳያወልቅ ውሎ እያደረ ካባ የሚያለብሰውን ልብሱን አወለቁበት፣ ሳይኖረው
የሚሰጠውን ቀሙት፣ በሞቱ የሚያኖረውን፣ በደሙ ቁስል የሚያሽረውን፣ በላቡ መከራ የሚያስቀረውን አሰቃዩት፡፡
የተከዱት ጀግኖች በፍጹም ልብ አምነው ነበር። ከተወደደች ሀገራቸው፣ አደራ ከሰጣቸው ሕዝባቸው፣ ምልክት እና ቃል ኪዳን ከኾነች
ሠንደቃቸው ያለፈ የሚያስቡት፣ የሚያስቡለት፣ የሚጠብቁት፣ የሚያስጠብቁት፣ የሚያስቀድሙት፣ የሚሳሱለት አንዳች ነገር የላቸውም፡፡
ማን አለ እንደ ወታደር ሀገሩን የሚወዳት? በቀበሮ ጉድጓድ ውሎ በቀበሮ ጉድጓድ የሚያድርላት? ማን አለ እንደ ወታደር ሀገሩን የሚያስብላት?
ከእናት ከአባቱ አስበልጦ የሚጨነቅላት? ማን አለ እንደ ወታደር ለሀገሩ ያለውን የሚሰጣት? በሞቱ መኖርን የሚያድላት? በአጥንቱ የሚያቆማት፣ በደሙ የሚያጸናት? ማን አለ እንደ ወታደር ሠንደቁን የሚያፈቅራት? እኔን ከአንቺ በላይ ያስቀድመኝ የሚላት? ማን አለ እንደ
ወታደር ለሀገሩ የሚዘምርላት? ከራስ በላይ ለሀገር እና ለሕዝብ እያለ የሚወድቅላት? እየሞቱ ማፍቀር እንደ ምን ያለ ፍቅር ነው? እየደሙ መውደድ እንደ ምን ያለ መውደድ ነው? እየተካዱ ማመን እንደ ምን ያለ እምነት ነው? እየተወጉ ይቅርታ ማድረግ እንደ ምን ያለ ይቅርታ ነው?
ጥቅምት 24 በታሰበች ቁጥር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሕገወጡ ሕወሃት የደረሰበት ክህደት ትታሰባለች፡፡ በዚህች ቀን ለዓመታት ሕዝባቸውን የጠበቁ ጀግኖች በጠበቁት ሰው ተክደዋል፣ በዚህች ቀን ለዓመታት ዐይናቸውን እርግብ ሳያደርጉ ለሕዝብ ክብር የቆሙ ከጀርባ
ተወግተዋል፡፡ በዚህች ቀን ሀገሬን እና ሕዝቤን ብሎ የወጣው የእናት አባቱን ፍቅር ጥሎ በድንበር የተሠባሠበው የሀገር መከላከለያ ሠራዊት የግፍ ግፍ ተፈጽሞበታል፡፡ ጠላቱን ሲጠብቅ ወዳጅ ገድሎታል፣ በፊቱ የሚመጣውን ሲመለከት በኋላው ተወግቷል፡፡
እኒያን ጀግና የኢትዮጵያ ወታደሮች ያሠባሠባቸው የሀገር ፍቅር፣ አንድ ያደረጋቸው የሠንደቅ ክብር ነው እንጂ ምንም አይደለም፡፡ በአንዲት ኢትዮጵያ ያምናሉ፣ በኢትዮጵያዊነት የጋራ ቤት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ታዲያ እንዲህ ሲኖሩ ሳለ ተከዱ፣ ተወጉ፡፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም
ኢትዮጵያዊያን ልብን የሚሰበር ዜና የሰሙበት፣ የኢትዮጵያ እናቶች የልጆቻቸውን የግፍ ሞት እያሰቡ ያለቀሱበት፣ ፊታቸውን እየነጩ የእንባ ጎርፍ ያፈሰሱበት ነበር፡፡ በዚህች ቀን የወታደር ልጆች የአባት እና የእናታቸውን ሞት በሰቆቃ ውስጥ አይተዋል፡፡ በዚህች ቀን ያጎረሱ እጆች ተነክሰዋል፡፡
ሁሉ እንዳልነበራቸው ባይተዋር ኾነው ቀርተዋል፡፡ የመከራ ጊዜን አሳልፈዋል፡፡ በዚህች ቀን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ጥይት እንዳይባክን ተብለው መኪና ተነድቶባቸዋል፡፡ ልብስ ሳይለብሱ በራቁት ተጥለዋል፡፡ ስጋቸው በሚወዷት ሀገራቸው አፈር በክብር እንዳታርፍ ለአራዊት
ተሰጥተዋል፡፡ እህል ውኃ እንዳይቀምሱ ተደርገው በረሃብ እና በጥም ተቀጥተዋል፡፡ ሲያጭዱ፣ ሲከምሩ፣ ሲያበራዩ እና አምበጣ ሲያባርሩ የዋሉ ወታደሮች ለድካማቸው ካሳ ሞት ተሰጥተዋል፡፡ መሰቃዬትን ተሸልመዋል፡፡ በዚህች ቀን የተከዱ የኢትዮጵያ ጀግኖች ስለ ጸናች ሀገራቸው፣ ስለ
ገቧት ቃል ኪዳናቸው ሲሉ ራሳቸውን ተከላከለው የከዳቸውን ሕገወጥ ቡድን መትተዋል፣ የወጋቸውን ወግተዋል፤ በሀገራቸው ላይ የተነሳውን ቀጥተዋል፡፡ አንገታቸውን ደፍተው፣ አልቅሰው እና ተክዘው አልቀሩም፡፡ ይባስ ብሎ መከራ አጠንክሯቸው፣ መገፋት እና መወጋት ከጀግንነት ላይ
ጀግንነት ደራርቦላቸው ተነሱ እንጂ፡፡ አጻፋውን መልሰው በቀናት ልዩነት ውስጥ የካዳቸውን ድል መቱት፡፡ የወሰደባቸውን ሁሉ ተቀበሉት፡፡ የኢትዮጵያን ጀግኖች ማንም ሰብሮ እንደማያስቀራቸው አሳዩት፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ሲከዳ እና ከኋላ ሲወጋ መለዮ የለበሰው
ብቻ አይደለም፤ መለዮ ያለበሰው ኢትዮጵያዊውም ተቆጥቶ ተነስቷል፡፡ ለሚመካበት እና ለሚኮራበት ወታደር ፈጥኖ ደርሷል፡፡ ከሞት የተረፈው፣ ከክህደት ያመለጠው ጀግና ወታደርም ነፍጡን አዙሮ የከዳውን ቀጥቶ ሀገር አደላድሏል፤ የጀግንነቱን ወሰን አረጋግጧል፡፡ ጥቅምት 24 ስትታሰብ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የከበረ ጀግንነትም ይታሰባል፡፡ ለምን ቢሉ የግፍ ግፍ ደርሶበት፣ ባመነው ተክዶ አንገቱን ደፍቶ አልቀረምና፤ አንድነቱን አጠናክሮ ለበለጠ ግዳጅ የተነሳበት እና የላቀ ድል ያስመዘገበበት ነውና፡፡ ይህች ቀን ግፍ የሚታሰብባት፣ መከዳት፣ አለመታመን
የሚወገዝባት፣ ክፉ አድራጊዎች የሚነቀፉባት እና የሚመከሩባት ናት፡፡ ይቅርታ ያደረጉ ልቦች የሚደነቁባት፣ የሚከበሩባት፣ የሚመሰገኑባት፣ ከፍ ከፍም የሚደረጉባት ቀንም ናት፡፡ ለውድ ሀገራችሁ ደም እና አጥንት የሰጣችሁ፣ ለተከበረች ሠንደቃችሁ የታመናችሁ የማይተካ ሕይወት
የሰጣችሁ ጀግኖች ኾይ ክብር ይገባችኋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበክልሉ የንግድ ሥራ ፈቃድ እድሳት ሙሉ በሙሉ በኦንላይን መስጠት ተጀመረ።
Next articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን ዓለም አቀፍ ምደባ አገኘ።