
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አሰጣጥን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምትኩ መስፍን የአማራ ክልል መንግሥት አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ ጊዜ እና ወጪን በሚቆጥብ መልኩ ለመስጠት የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን በስፋት እየተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በኦንላይን (Online) መስጠት መጀመሩን ነው የገለጹት። የንግድ ሥራ ፈቃድ እድሳት ከሐምሌ 01/2018 እስከ ታኅሣሥ 30/2019 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ያለምንም ቅጣት የሚከናወን መኾኑንም ተናግረዋል።
በዚህ በጀት ዓመት በኦንላይን 380 ሺህ የንግድ ሥራ ፈቃዶችን ለማደስ መታቀዱንም አመላክተዋል። እስከ አሁን ባለው ሂደትም 92 ሺህ የሚጠጉ ፈቃዶች በኦንላይን መታደሳቸውን ነው የጠቀሱት።
ነጋዴዎች ጊዜ አለኝ በሚል እሳቤ እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ የመዘግየት ልማድ እንዳላቸው ያነሱት ዳይሬክተሩ ያለ ቅጣት በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ፈቃድን አድሶ በነፃነት ሥራን ከመሥራት አንፃር ትልቅ ክፍተት እየፈጠረ እንደኾነም ተናግረዋል። ጊዜውን አልፈው ከታኅሣሥ 30/2019 ዓ.ም በኋላ ለሚያድሱ ነጋዴዎች የቅጣት ሥርዓቱ በጥር ወር 2ሺህ 500 ብር እንደኾነ ገልጸዋል።
የካቲት ወር ላይ እና ከዚያ በኋላ ባሉ ወራት ደግሞ በየወሩ ከ2ሺህ 500 ብር በተጨማሪ 1 ሺህ 500 ብር እየተጨመረ ይሄዳል ብለዋል። ከሰኔ 30 በኋላ ቅጣቱ እስከ 20 ሺህ ብር እንደሚደርስም አመላክተዋል።
ለዚህም ነጋዴው ተጨማሪ ወጪ እና እንግልት ውስጥ ሳይገባ በሰዓቱ በኦንላይን አገልግሎቱን መጠቀም እንደሚገባው አጽንዖት ሰጥተዋል። ሲስተሙ ሙሉ በሙሉ በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከፌስቡክ እና ቴሌግራም መተግበሪያዎች ባነሰ መልኩ በቀላሉ የሚመራ በመኾኑ ማንኛውም ማንበብ የሚችል ሰው በራሱ ስልክ ወይም በኢንተርኔት ካፌዎች መጠቀም ይችላል ብለዋል። ባለፈው ዓመት የፌዴራል እና የክልሉ ሰርቨር አንድ ላይ በመኾኑ የተወሰኑ መስተጓጎሎች እንደነበሩ ያስታወሱት ዳይሬክተሩ በዚህ ዓመት ንግድ ሚኒስቴር ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ ሰርቨሩን በማስተካከሉ የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የሚቸገሩ ወይም የኢንተርኔት አማራጭ የማይኖራቸው የንግዱ ማኅበረሰቦች በወረዳ ደረጃ ያሉ የቢሮው ሙያተኞች ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸውም ገልጸዋል። የክፍያ ኮዶች በሰዓቱ ወደ እጅ ስልክ ሲላኩ በቴሌብር ወይም በባንክ በኩል ክፍያውን ፈጽመው ሰርተፊኬቱን ማግኘት እንደሚችሉም ተናግረዋል።
ከአዲስ ፈቃድ እና ምዝገባ አኳያ በበጀት ዓመቱ የታቀደውን ያህል ውጤት ማምጣት እንደተቻለም ገልጸዋል። ከአዲስ ፈቃድ አንፃር ከታቀደው 49 ሺህ ውስጥ 47 ሺህ ማከናወን እንደተቻለም ተናግረዋል።
ግብር በመክፈል ሂደት ውስጥ ከ96 ሺህ አገልግሎት ጠያቂዎች 54 ሺህ በላይ የሚኾኑት ከክፍያ ነፃ በኾነ መልኩ አገልግሎቱን አግኝተዋልም ብለዋል። ባለፈው ዓመት እንደነበረው የጊዜ ገደብ መራዘም ዘንድሮም ይኖራል የሚል እሳቤ ፈጽሞ ሊኖር እንደማይገባ ተናግረዋል።
ሕጉ እንደሚለው እስከ ታኅሣሥ 30 ያለው ጊዜ ጥብቅ መኾኑ ታውቆ ሁሉም ነጋዴ ከወዲሁ ፈቃዱን ማደስ አለበት ብለዋል። ከታኅሣሥ 30/2019 ዓ.ም በኋላ የሚቆዩ በቢሮው በኩል ተከታትሎ የሚጣራባቸው በመኾኑ የንግዱ ማኅበረሰብ ከወዲሁ ወደ ሕጋዊ እና ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት በመግባት ከቅጣት እራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸውም ቢሮው አሳስቧል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_24_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
