“በጋራ ክልላዊ ሁኔታችን ላይ ማተኮር አለብን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

9

 

የአማራ ክልል የ2019 በጀት ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።

በግምገማ መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ግምገማው የተቋማትን የመፈጸም አቅም የምንፈትሽበት እና ተቋማትን የሚመሩ መሪዎችን ውጤታማነት በጋራ የምናይበት ነው ብለዋል። በአፈጻጸም ሂደት የታዩ ጥንካሬዎችን እና ውስንነቶችን በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጡም ገልጸዋል።

የሥራ አፈጻጸሙን በትኩረት እንደሚገመግሙ የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ “የሥራ አፈጻጸማችን የሚገመገመው ከስትራቴጂክ ግባችን አንጻር ነው” ብለዋል። መሪዎች ስትራቴጂካዊ ግቦችን መሠረት አድርገው መሥራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግሥት አፈጻጸሙን የሚገመግመው ከረጅም ጊዜ ካቀደው ዕቅድ አኳያ ነው ብለዋል። ዕቅዱ ችግሮችን እና መልካም ዕድሎችን ታሳቢ አድርጎ መታቀዱንም አስታውሰዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት የ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ማቀዱን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ በእነዚህ ዓመታት ማሳካት ያሰብናቸውን ግቦች እና መዳረሻዎች ታሳቢ በማድረግ መሥራት ይገባናል ነው ያሉት። መሪዎች ምርታማነትን ማሳደግ እና አገልግሎትን ማቀላጠፍ ይገባቸዋልም ብለዋል።

ለሚቀጥሉት ጊዜያት መነሻ የሚኾን ግምገማ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። አርቆ ማየት እና አልቆ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የጋራ የለውጥ ፍላጎታችንን ማሳካት በሚያስችል ሁኔታ አፈጻጸማችንን መገምገም ያስፈልገናል ነው ያሉት።

በጋራ ክልላዊ ሁኔታችን ላይ ማተኮር አለብን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የጋራ ጥንካሬያችን እና የጋራ ውስንነቶቻችን ምንድን ናቸው የሚለውን በትኩረት መገምገም አለብን ብለዋል። ጥንካሬዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ውስንነቶችን ለማረም የሚያስችል ግምገማ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በሚቀጥሉት ወራት ስኬታማ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ግምገማ ማድረግ አለብንም ብለዋል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_24_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article«ተጸጽተናል፤ ባለዕዳም ኾነናል፤ የበደልነውን እንክሳለን» የቀድሞ ታጣቂዎች
Next articleበክልሉ የንግድ ሥራ ፈቃድ እድሳት ሙሉ በሙሉ በኦንላይን መስጠት ተጀመረ።