«ተጸጽተናል፤ ባለዕዳም ኾነናል፤ የበደልነውን እንክሳለን» የቀድሞ ታጣቂዎች

29
በአማራ ክልል እየታየ ያለው ሰላም ለሕዝብ ልማቶች እና እድገት ትልቅ ተስፋ እየኾነ መጥቷል። የሰላም እጦቱ ያደረሰው ኪሳራ ዘርፈ ብዙ ነው። ይህን ጉዳት የተገነዘቡ እና የክልሉ ልማት ያሳሰባቸው የቀድሞ ታጣቂዎች፤ የተዘረጉትን የሰላም እጆች መጨበጣቸውን ቀጥለዋል። በርካታ
የቀድሞ ታጣቂዎች ሰላምን መርጠው ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሕይዎታቸው እየተመለሱ ይገኛሉ።በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም መንገድን የተከተሉ የቀድሞ ታጣቂዎች እንደተናገሩት ሕዝቡን ሲበድሉ መቆየታቸውን በጸጸት መለስ ብለው ያስታውሳሉ። የጫካ ሕይወት ፈታኝ፣ የሕሊና
ጸጸት ያለው እና ባለዕዳ እንደሚያደርግም ይናገራሉ፤ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመከተላቸውም ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።ወደ ሰላም ከተመለሱ በኋላም የተሃድሶ ሥልጠና መውሰዳቸውንም ነግረውናል፤ በዚህ ድርጊታቸው ተጸጽተው መንግሥትን እና ሕዝብን ለመካስ ሰላምን
መምረጣቸውን አንስተው አሁን ላይ ሕዝብን እና መንግሥትን በቅንነት እያገለገሉ መኾናቸውን አስረድተዋል።አንዳንዶችም መንግሥት ባመቻቸላቸው የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ በመኾን የተረጋጋ ሕይወት እየመሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። «አሁን ላይ እኛም
ማኅበረሰቡም እፎይታ አግኝተናል» ያሉት የቀድሞ ታጣቂዎች፤ የጫካው ሕይወት አስቸጋሪ መኾኑን አንስተዋል። የሰላም መንገዶችን መከተል ፍሬው ጣፋጭ ሲኾን፣ የጫካ ሕይወት ግን እረፍት የሚነሳ መኾኑን ገልጸው፤ ሌሎችም የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
በክልሉ የሰላም አማራጭ የሚከተሉ ቡድኖች እና ግለሰቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸው፣ በክልሉ የተረጋጋ ሕይወት እንዲፈጠር ከማድረጉም በላይ ልማት እንዲፋጠን እና የማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ትልቅ ዕድል ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ መንግሥት መሥረታ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ በግጭት እና በጠላትነት የሚገኝ ትርፍ የለም ብለዋል። መሣሪያ አንሥተው በጫካ የሚገኙ አካላት የተዘረጋውን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
አሁንም የሰላም ደወል በጎላ ድምጽ መደወሉን ቀጥሏል። ሰላምን ቀዳሚ ምርጫ ማድረግ ልማትን ለማፋጠን እና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። ይህም የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ እንደሚያግዝም ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበባሕር ዳር የሕዝብን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
Next article“በጋራ ክልላዊ ሁኔታችን ላይ ማተኮር አለብን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ