
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣ 14ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 33ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ጌትነት እውነቱ (ዶ.ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ከተማዋ በታሪኳ የመጀመሪያ በኾነ መልኩ
ሁለንተናዊ ልማቶችን በማፋጠን የሕዝብን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።
አፈ ጉባኤው በተያዘው በጀት ዓመትም ለልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። የከተማዋን ሁለገብ
ልማት እና ሰላም ይበልጥ ለማስፋት ነዋሪዎች በየአካባቢያቸው ንቁ ተሳትፎ እና ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል። ምክር ቤቱ ከአስፈፃሚ እና የጸጥታ አካላት ክትትል እና ቁጥጥር አኳያ በ2018 በጀት ዓመት በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል። በዚህም የመሠረተ ልማት ግንባታዎች
ጥራት እና ደረጃ ተጠብቆ በተያዘላቸው ጊዜ እና ሀብት እንዲጠናቀቁ ድጋፍ ተደርጓልም ነው ያሉት።በተጨማሪም የምክር ቤቱ ሥራዎች ከአሥተዳደራዊ እና ሕዝባዊ ጉዳዮች ጋር ተቀናጅተው ስለመሠራታቸውም ነው የጠቆሙት። ለአቤቱታ አቅራቢዎችም ተገቢው ምላሽ ተሰጥቷል፤
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የአደረጃጀት መሪዎች አማካኝነት ከተደረገ ውይይት ጋር ተያይዞ የመኖሪያ ቤት ቦታ መመሪያ ጥያቄ ላነሱ 80 ቅሬታ አቅራቢዎች መፍትሄ ተሰጥቶ የቦታ ባለቤት እንዲኾኑ ተመቻችቷልም ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
