
ኢትዮጵያ በታሪኳ የሉዓላዊነት ተምሳሌት የኾነች ሀገር ናት። ለጎረቤቶቿ የሰላም ጋሻ በመኾንም አስተዋጽኦ አበርክታለች። የሰላም ማስከበር ላይ የሠራችው ሥራም ለጎረቤቶቿ የሰላም ጋሻ መኾኗ አንዱ ማሳያ ነው። ኃያል ሀገርም አድርጓታል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ
ኅብረት ጥላ ስር በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በብሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን (አብዬ) እና በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር መስዋዕትነት ከከፈሉ ቀዳሚ ሀገራት አንዷ መኾኗንም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር መረጃ ያመላክታል። ያደረገችው የፀረ ሽብር ትግልም ሌላው የጎረቤት ሀገራት
የሰላም ጋሻ መኾኗን የሚያሳይ ተግባር ነው። በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በተለይም በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አልሸባብ የተባለውን አሸባሪ ቡድን በመዋጋት እና የቀጣናውን ደኅንነት በማስጠበቅ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች። የኢኮኖሚ ትስስር እና ልማት ላይ የሠራችው ሥራም
ለጎረቤት ሀገራትም ተስፋ የሰጠ ተግባር ነው። እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለጎረቤት ሀገራት ታዳሽ ኀይል በማቅረብ የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው።
አንደኛው ጉዳይ የባሕር በር ይገባኛል ጥያቄ እና የጂኦፖለቲካ ውጥረት በአንዳንድ ሀገራት እና ፖለቲከኞች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል። ንጋቱ ቆጪቶ “የኢትዮጵያ ባሕር በር አልባነት እና ለብሔራዊ ደኅንነት ያለው አንድምታ፤ ፈተናዎች እና ተስፋዎች” በሚል በሠሩት ጥናት እንዳመላከቱት
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት እንደ ሉዓላዊነት መደፈር ተቆጥሯል። ይህም በቀጣናው ላይ አዲስ የዲፕሎማሲ እና የደኅንነት ስጋት ፈጥሯል። የኢትዮጵያ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ይፋዊ መግለጫዎች እንደሚያስረዱት የሕዳሴው ግድብ ግንባታ እና የውኃ
አሞላል ሂደቱ በታችኞቹ የናይል ተፋሰስ ሀገራት (በተለይም በግብጽ እና በተወሰነ መልኩ በሱዳን) ላይ የውኃ እጥረት ያስከትላል በሚል የተሳሳተ አመለካከት ከፍተኛ የስጋት እና የፖለቲካ አለመግባባት ምንጭ ኾኖ ቆይቷል። በጥቅሉ የኢትዮጵያ ኀያልነት ለቀጣናው ተስፋ ወይስ
ስጋት ? የሚለው ጥያቄ መልሱ ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ የቀጣናው የሰላም ጋሻ እንጂ ስጋት ኾና እንደማታውቅ የቀረቡት መረጃዎች ያስረዳሉ። ጥቂት ሀገራት ግን ለብቻ ለመጠቀም ካለ ፍላጎት እና የወቅቱ ፖለቲካዊ አሰላለፍ ሲቀያየር በስጋት መመልከት ይኖራል፤ የሚጠበቅም ነው።
ኢትዮጵያ ግን ሁሌም የጎረቤቶቿ ደኅንነት አስጠባቂ ናትና መቸም ስጋት ሁና አታውቅም ወደፊትም አትኾንም።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
