
የሲሪንቃ የግብርና ምርምር ማዕከል በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ ተቋም ነው። ማዕከሉ በተለይም በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደርን የሚያካልሉ ሰፊ አካባቢዎችን ይደግፋል።
የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ስዩም አሰፌ (ዶ.ር) ለአሚኮ እንደተናገሩት በአካባቢው የግብርና ምርት እና ምርታማነትን ለማሻሻል በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በዘር ብዜት፣ በአፈር እና ውኃ ጥበቃ፣ በደን ልማት፣ በማኅበራዊ ስርጸት እና በግብርና ኤክስቴንሽን ዘርፎች ማዕከል አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
አካባቢዎችን መሠረት ባደረገ መልኩ ከቆላ እስከ ደጋ የሚስማሙ የተሻሻሉ የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎችን በማላመድ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
በማዕከሉ የምርምር ውጤቶች ከ68 በላይ የሰብል ዝርያዎች መለቀቃቸውን ተናግረዋል። በኩታ ገጠም የማምረት ዘዴን ለአካባቢው ማኅበረሰብ አስተዋውቆ በውጤታማነት ወደ ሥራ አስገብቷል ነው ያሉት ።
ለአብነትም በባቄላ፣ በስንዴ፣ በጤፍ፣ በበቆሎ፣ በገብስ እና በምስር ሰብሎች ከመቄት እስከ ወረኢሉ እና ጃማ ደጎሎ ወረዳዎች በስፋት እየሠራ ነው ብለዋል። በቆላማ አካባቢዎችም ከቆቦ እስከ ባቲ እና ሸዋ ሮቢት ድረስ በማሽላ፣ በማሾ፣ በአኩሪ አተር፣ በቦለቄ፣ በአትክልት እና በፍራፍሬ ልማት እያገዘ ነው ብለዋል።
ከ100 በላይ የምርምር ሥራዎችን በአርሶ አደሮች ማሳ እና በሠርቶ ማሳያ ምርምር ማዕከላት አጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት። በእንስሳት ልማት ዘርፍም የተሻሻሉ የ”ዶርፐር” የበግ ዝርያዎችን በማዳቀል ከ500 በላይ የተዳቀሉ በጎችን ማራባት እንደተቻለም አንስተዋል።
በተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች ከ50 ሄክታር መሬት ላይ የቅድመ መሥራች ዘር እና ከ10 ሄክታር በላይ በአራቢ ዘሮች በማባዛት ለአርሶ አደሮች እንደሚሠራጭም አንስተዋል። በቅርቡም 8 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ማከፋፈል መቻሉንም ጠቁመዋል።
ተቋሙ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ጉዳት ደርሶበት እንደነበር የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ ወደ ነበረበት የተሟላ አቅም እንዲመለስ እና የተሻለ የምርምር ማዕከል እንዲኾን አጋር እና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
