ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የተደረገ አጋርነት፤ የዳንግላ ወረዳ አበረታች ድጋፍ።

4
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የዳንግላ ወረዳ ሀገራዊ ግዳጁን በብቃት እየተወጣ ለሚገኘው የምሥራቅ ዕዝ ኮር ሠራዊት አጋርነቱን ለማሳየት እና የሞራል ድጋፍ መስጠት የሚያስችል የዕርድ ሰንጋ ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን ያስረከቡት የዳንግላ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሙሀቤ ጸጋው ሠራዊቱ ለሀገር ሰላም፣ ሉዓላዊነት እና ደኅንነት ሲባል የሚከፍለው መስዋዕትነት ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ነው ብለዋል። ሠራዊቱ ቀን እና ማታ ለሀገር ሕልውና እና ለሕዝብ ሰላም ሲል እጅግ ውድ የኾነ ሕይወቱን እየከፈለ ይገኛል ነው ያሉት።
እኛም የሕዝብ ልጆች እንደመኾናችን መጠን ሠራዊቱ የሚገኝበትን የትግል አውድ በመረዳት የዕለት ከዕለት ውሎውን በማሰብ ይህንን የዕርድ ሰንጋ ድጋፍ አበርክተናል ብለዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የምሥራቅ ዕዝ ኮር ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮሎኔል ልጃለም ምትኩ ከሕዝቡ የተደረገልን ድጋፍ የሠራዊቱን ሞራል ከፍ የሚያደርግ እንደኾነ ገልጸዋል። ሠራዊቱን እና ሕዝቡን ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ መኾኑንም አንስተዋል።
ሠራዊቱ የሕዝብ አደራ በመሸከም የተጣለበትን ሀገራዊ ግዳጅ በብቃት እየተወጣ ነው ብለዋል። ደጀኑ ሕዝብም ከሠራዊታችን ጎን በመቆም ላደረገልን ድጋፍ እናመሰግናለን ነው ያሉት። መረጃው የምሥራቅ ዕዝ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከመቄት እስከ ጃማ ደጎሎ፣ ከቆቦ እስከ ባቲ የተዘረጋው የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል የልማት አውታር