ሁሌም ከጠላቶቿ በላይ የምትውለው ታላቋ ኢትዮጵያ!🇪🇹

3

 

ኢትዮጵያ በታሪኳ አያሌ ፈተናዎችን አሳልፋለች። የሉዓላዊነቷ እና የብሔራዊ ደኅንነቷ ፈተናዎች ከውጭ ጠላቶቿ እና ከውስጥ የባንዳ ኀይሎች ግንኙነት የሚመጣ ነው።

በተለይም የቀጣናው የኀይል ፍላጎት እየተቀያየረ በሚገኙበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያን የቀጣናው የደኅንነት ወሳኝ ማዕከል እንድትኾን አድርጓታል። በአንጻሩ ፍላጎቶቻቸውን ከጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ጋር በማስተሳሰር ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚጥሩ የውጭ ኀይሎችም በሀገሪቱ ላይ የሚጠነስሱት ሴራ ቀጥሏል።

ግብጽ በቀጣናው ያላትን ተጽዕኖ ለማስፋት እና የውኃ ፖለቲካዋን ለማስጠበቅ ከአስመራ ጋር የምታደርገው ከንቱ ጥምረት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ፍላጎቶች በተቃርኖ የቆመ ነው። ኤርትራም ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት እና በቀጣናው ጎልታ እንዳትወጣ ባላት ፍላጎት የሁለቱ ሀገራት አሰላለፍን በአንድ መሥመር ላይ አገናኝቷቸዋል።

በሌላ በኩል የውጭ ጠላቶች ሴራቸውን ለማስፈጸም የውስጥ ባንዳ ተባባሪዎችን ይጠቀማሉ፤ ሀገርን ከውስጥ የመረበሽ ስልትን ቀጥለውበታል። ነገር ግን ኢትዮጵያ የሚጋረጡባትን የጠላት አሰላለፎች በመበጣጠስ ሁሌም በአሸናፊነት የሚደመደም ታሪክ ያላት ሀገር ናት።

የኢትዮጵያ ዝግጁነትም ማንኛውንም ውጫዊ እና ውስጣዊ ጥቃት ለመቀልበስ በሚያስችል ተግባራዊ ብቃት ላይ የተመሠረተ ነው። የቀደመ ታሪኳም የሚያስረዳው ይህንን ነው፤ አሁናዊ ዝግጅቷም ከቀደመው የላቀ ነው።

የጋራ ጠላቶቿን ሴራ እየበጣጠሰች ዛሬም በዲፕሎማሲ፣ በጸጥታ እና በፖለቲካ መስኮች ሁሉን አቀፍ ዝግጁነት ላይ ትገኛለች። የሀገሪቱ ሉዓላዊነት የማይደፈር፣ ብሔራዊ ጥቅሟም በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠበቅበት ምዕራፍም ላይ ትገኛለች።

የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀ፣ ውጊያ በአጭር ጊዜ መጨረስ የሚችል እና በከፍተኛ ሥነ ምግባር የታነጸ ኀይል ኾኖ ተደራጅቷል። የሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ እና የፖለቲካ መሪዎችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ።

የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት ከካርቱም እስከ አስመራ፣ ከካይሮ እስከ ሀገር ውስጥ ጠላቶች የተጠነሰሰውን የጥፋት ተልዕኮ ሠራዊቱ በብቃት እያመከነው ይገኛል። ዛሬም የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል ሁልጊዜም ዝግጁ መኾኑን አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) “ኢትዮጵያ በብዙ ጠላቶች የተከበበች ሀገር ናት” ብለዋል። የአየር ክልላችን እንዳይደፈር በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ለዚህም ዘመናዊ የጦር ጀቶችን ጭምር እየታጠቀች አቅሟን እያጠናከረች መኾኑን ተናግረዋል።

እነዚህን መሠል የውጊያ ቴክኖሎጂዎች በመታጠቅ ከሰሃራ በታች ካሉት ሀገራት የመጀመሪዋ የኾነችው ኢትዮጵያ ራሷን የመከላከል አቅሟን በከፍተኛ ደረጃ እየገነባች መኾኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

#የመደመር_መንግሥት
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_22_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleባዲገዝ – የወሎየዎች ተሳስቦ የመኖር አንዱ እሴት
Next article🌾የአርሶ አደር ሠርቶ ማሳያዎች – ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለምርት እድገት ምሶሶዎች