ባዲገዝ – የወሎየዎች ተሳስቦ የመኖር አንዱ እሴት

5

 

ዓመታዊ የእሸት ቅመሱ ሳምንት “ባዲገዝ” በየዓመቱ በጥቅምት አጋማሽ የሚካሄድ ልዩ ዝግጅት ነው። በቆሎ፣ ባቄላ፣ ጥንቅሽ፣ ዱባ፣ ማር፣ እርጎን ጨምሮ የአርሶ አደሮች የላብ ውጤቶች በአንድ ቦታ ቀርበው ሁሉም የፈለገውን እና ያማረውን የሚቋደስበት የማካፈል በዓል ነው።

በዝግጅቱ ያላረሱ ወገኖች እሸትን እንደልባቸው ይቀምሳሉ። በዓሉ ያለው ለሌለው የማካፈል ምሳሌ ነው። በቦታው ተገኝቶ አምሮትን ከማውጣት በተጨማሪ ስለ ሀገር ሰላም እና እድገት ዱዓ (ፀሎት) የሚደረግበት መድረክም ነው።

የዘንድሮው የ”ባዲገዝ” የእሸት ቅመሱ ሳምንት በኮምቦልቻ ከተማ በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።

አሚኮ ያነጋገራቸው በበዓሉ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኮምቦልቻ ከተማ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ተሾመ በላይ በዝግጅቱ ላይ መሳተፍ ከጀመሩ 13 ዓመት ማስቆጠራቸውን ገልጸውልናል።

“ባዲገዝ የወሎን ነባር ባሕል የሚያንፀባርቅ ነው። በባሕላችን እሸት ሲደርስ ተካፍሎ የመብላት ባሕል ነበር። “ባዲገዝ” ደግሞ ያንን አጠናክሮ አስቀጥሏል” ነው ያሉት።

ሌላኛው የበዓሉ ተሳታፊ ሰይድ ይመር የእሸት ሳምንቱ ከረጅም ጊዜ በፊት በትንሽ ነገር መጀመሩን አስታውሰው አሁን በርካታ ሕዝብ የሚሳተፍበት በዓል መኾኑን ይጠቅሳሉ።

“ልጅ እያለን አባቶቻችን አዝመራ ውስጥ ሁነን ጥንቅሽ እየበላን ሰው ሲያልፍ ከተመለከትን ቆርጠን እንድንሰጥ እና እንድናካፍል ትዕዛዝ ይሰጡን ነበር። ባዲገዝም ሰው ባለው ልክ ተካፍሎ እንዲበላ ያደርግ የነበረውን፣ ሊጠፋ ያለውን ባሕላችንን ያስቀጠለ ነው” ብለዋል።

የሚያዋድዱ እና ማንነታችንን የሚያስተዋውቁ ባሕሎቻችን መጠናከር እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የ”ባዲገዝ” የእሸት ቅመሱ ዝግጅት በሐጂ አሊ ሽፋው አስተባባሪነት እየተመራ አራት አስርት ዓመታትን ተሻግሯል።

ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ “ባዲገዝን” ማዘጋጀት መጀመራቸውን የሚገልጹት ሐጂ አሊ ሺፋው አሮጌው እህል አልቆ አዲሱ እህል መግባቱ የሚበሰርበት ነው ብለውናል።

ባዲገዝ “ባዕድ ይገዝ” የሚል ትርጉም አለው ያሉን ሲኾን፤ ዘመድ ያልኾነ መጥቶ እሸት በልቶ ሀገር ሰላም እንድትኾን በዱአ ያግዝ ማለት መኾኑን ገልጸዋል።

በዓሉ አብሮ የመብላት፣ የአንድነት እና የሰላም ተምሳሌት መኾኑንም ጠቅሰዋል።

«ፍቅርን ሽጠን ፍቅርን የምንገዛበት በዓል ኾኗል፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ» ነው ያሉት።

ወደፊት ይህ መልካም እሴት እንዳይጠፋ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በየኔነት መንፈስ ባለው አቅም ሁሉ እንዲያግዝም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ መሬማ አሊ “ባዲገዝ”ን በተከታታይ ዓመታት ሕዝቡ በየኔነት ስሜት እሴቱን ጠብቆ እያከበረው ይገኛልም ብለዋል።

ለትውልዱ ተካፍሎ መኖርን እና አንድነትን ከማስተላለፍ አንፃር በዓሉ ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት። እንደተቋምም ዓመታዊው የእሸት ቅመሱ በዓል እንዳይስተጓጎል እያገዝን ነው ብለዋል።

እሴቱ ቀጣይነት እንዲኖረው እና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ደሴ #ጥቅምት_22_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:- መስዑድ ጀማል

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleክንደ-ብረት፣ ልበ-አንበሳ – የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት!
Next articleሁሌም ከጠላቶቿ በላይ የምትውለው ታላቋ ኢትዮጵያ!🇪🇹